ከዝንብ ማር አንጠብቅም
ሚሊዮን ጎሣዬ (ከኦስሎ - ኖርዌይ)
አይሆንም እንጂ ቢሆንና ዝንብ ማር መስጠት ብትጀምር ከአዲስ አበባ አካባቢዎች እንደ ተክለኃይማኖትና መርካቶ ማርን በብዛት የሚያመርት ይኖራል ብዬ አልገምትም። ለምን? ቢሉ አዲስ አበባ ምን ትላለች እኔም አፍንጫ የለኝም ነው ያለው ጋሽ ስብሃት። እውነታው ግን ዝንብም ማር ሰጥታ አታውቅም፤ ወያኔም ዴሞክራሲያዊ ምርጫን።
ከዘንድሮ ምርጫ የተለየ ነገር የጠበቀ ካለ እሱ ሞኝ አልያም የዋህ ተስፈኛ ነው። እኔን ግን የማይገባኝ ህዝባችንን ለምን እንደማይተዉት ነው። ምርጫ እያሉ በሞራሉ በገንዘቡና በጊዜው ለምን እንደሚቀልዱበት ነው ያልገባኝ።
አምባገነን መሆናቸውን ጠንቅቀን አውቀናል። ታድያ ለምን ምርጫ እያሉ ያደክሙናል። ለነገሩ ባለንበት ወቅት ሁሉ ነገር ዘምኖ የለ እንዴ? ... መኪናው፣ ስልኩ፣ ቤቱ፣ ... ብለን መዘረዘር አያስፈልገንም። ከቁሳቁሱም አልፎ ንግግርና እስከ አስተሳሰብ ድረስ እጅግ ዘምኖአል። የኛም ጠቅላይ ሚንስትር በባለቤትነት አዘምነው የፈጠሩት አምባገነንነት አለ ምርጫ ልማትና ዴሞክራሲ በመሳሰሉ በወርቃማ ቃላት የተለበጠ ሆኖ፤ ህዝቡ በአንድነት እንዳይቃወም በመከፋፈል ለጋሽ ሀገራትን ማደናገርያ የምርጫ ድራማን በመሥራት ዕድሜን በሥልጣን ላይ ማቆት ነው። በዚህ ዘመናዊ አምባገነንት ስልት ለሃያ ዓመት መግዛቱ ሲገርመን ለሌላ አምስት ዓመት ሊቆይ ነው።
ዛሬ ዛሬ ንግግራቸው ስድብ ሆኖባቸው የተቸገሩት መሪያችን፤ የዘንድሮውን ምርጫ 99% አሸነፍኩ ብለው ህዝቡንና ምዕራባዊያንን ሊሰብኩ መስቀል አደባባይ ሲወጡ፤ እንደ ዴሞክራሲያዊ እና በህዝቡ 99% እንደተመረጠ መሪ በመስታወት ተሸፍነው ንግግር ሲያደርጉ አላኮሩአችሁም።
በዘንድሮው ምርጫ ወያኔ የተሸወደው ነገር ቢኖር ያጭበርበርው በሁሉም የሀገሪቱ የምርጫ ጣቢያዎች መሆኑ ነው። እንደእኔ ግምት ከሆነ እነሱ ሊያደርጉ ያሰቡት የነበረው በሁሉም የምርጫ ጣቢያ ድምፅ መስረቁ ሊሳካ አይችል ይሆናል የሚል ፍርሃት ስለነበራቸው ከሁሉም አብላጫውን ለመያዝ ተደራጅተው በሁሉም ምርጫ ጣቢያ በተለያየ ዘዴ እንደአስፈላጊነቱ ኃይልንም ጭምር በመጠቀም ድምፅን በመስረቅ ቢያንስ 70 እና 80 ከመቶውን ለመውሰድ አስበው ነበር የተንቀሳቀሱት።
ነገሩ ግን ያልጠበቁት ሆኖ ሌብነቱ ሁሉም ቦታ ተሳካላቸው፤ እናም አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ሆኖ ነገሩ ባላሰቡት ድል የተቃዋሚዎች ተቃዋሚ ሆነው ወዳጁ የነበሩትን እነ ልደቱን እንኳን ከጫወታ ውጪ አደረገበት። አይገርምም።
የነልደቱ ነገር ከተነሳ ጥቂት እንጨዋወት። በፓርላማው ላይ ሁሌ በድምፅ ብልጫ የሚሸነፍ መከራከሪያ ከሚያቀርቡት አንዱ የነበሩት አቶ ልደቱ፤ ከ97 ምርጫ በኋላ በህዝብ ዘንድ እንደ ከዳተኛ ተቆጥረው ነው የሚታዩት። ህዝብ ከጠላኝ ወደ መንግሥት ልጠጋ ብለው ከወያኔ አበሩ። ድጋሚ ተሸወዱ። ለሱ አግዘው ተቃዋሚዎችን በሙሉ ሲተቹና ወያኔን ሲደግፉ ከርመው ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሲያንቆለጳጵሷቸው ወደውኛልና ቢቻል ሥልጣን ካልሆነም ያቺውን የፓርላማ ወንበሬን አላጣም ብለው ሲኩራሩ ሳለ እንኳን ለሳቸው በፓርላማ ወንበር ለተወዳጁት ቀርቶ ለበረሃ ጓዶቹ ለአቶ ስዬና ለአቶ ታምራት ያልራራው አቶ መለስ ከጫወታ ውጪ ነህ አላቸው። ምንኛ ያሳዝናሉ ከህዝብ ቢወግኑ ኖሮ መከዳት አይኖርም ነበር።
ፓርላማው ሙሉ በሙሉ በወያኔ መያዙ ጥሩ ነው። ይህ የግሌ ሃሳብ ነው። ይቅርታ! እንዴት? ብትሉ ለኢትዮጵያዊውም ሆነ ለተቀረው ዓለም ትክክለኛ የወያኔን ማንነት ለማወቅ ያስችላል እላለሁ። በዛ ላይ አንድም ጊዜ በፓርላማ ውስጥ አሸንፎ ያልወጣው የተቃዋሚዎች ሃሳብና አስተያየት ወያኔን ዲሞክራሲያዊ መንግሥት አስመስሎት ቆይቷል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ ተቃዋሚዎች በአንድነት ለአንድ ዓላማ እንዲሠሩ ያደርጋቸው እንደሆን ብዬ አስባለሁ። በሌላ መልኩ ደግሞ ምዕራባዊያን ከባድ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ብዬ ባልጠብቅም፤ አሁን የሚመለከቱበት መነጽር ግን ከቀድሞው ሊለይ ይችላል ብዬ እገምታለሁ።
በመጨረሻ አንድ ነገር ልበልና ላብቃ። ኢዴፓ ባወጣው መግለጫ አንድ ቁም ነገር አስፍሯል። ምርጫው ቢመደገም ትርጉም እንደሌለው ገልጾ፣ ከዛ ይልቅ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ውይይት እንዲደረግ ጠይቋል። እንደግለሰብ የምደግፈው ሃሳብ ነው። የምርጫው መደገም ትርጉም ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ከዝንብ ማር አንጠብቅምና።
ሚሊዮን ጎሣዬ
ከኦስሎ - ኖርዌይ



