ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

የ2002 ምርጫ ሊደረግ ከአንድ ወር በታች ቀርቶታል። ገዢው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት ”ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲሆን ለማድረግ የነበረኝን ቁርጠኝነት እያሳየሁ ነው” ይላል። የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢዎችም ምርጫውን ለመታዘብ አዲስ አበባ ገብተዋል። መድረኩ ባለፉት ሦስት ሣምንታት ብቻ በመቱ፣ በወልቂጤ፣ በደብረ ብርሃን፣ በደሴ፣ በወልዲያ፣ በኮምቦልቻ እንዲሁም በተለያዩ የአዲስ አበባ ወረዳዎች ታላላቅ ህዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረገ ነው። በአቶ ኃይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ በአዋሳ፣ በአቶ ልደቱ የሚመራው ኢዴፓ ደግሞ በአለታ ወንዶ፣ ጎንደርና ባህር ዳር ህዝባዊ ስብሰባዎች ያደረገ ሲሆን፤ የምርጫ ዘመቻቸውን አጧጥፈውታል።

 

በሀገር ቤት ያለው ይሄን ሲመስል፤ በውጭ ሀገር በአንዳንድ ማዕዘናት ምርጫውን ቦይኮት የማድረግ (በምርጫው ያለመሳተፍ) ጥሪ እየቀረበ ነው። የግንቦት ሰባትን ንቅናቄ ደጋፊዎችን ጨምሮ አንዳንድ የተቃዋሚ ወገኖች ”ምርጫውን ህወሓት/ኢህአዴግ አሸንፎታል። ከምርጫው እራስን ማግለል ያስፈልጋል” የሚል የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከከፈቱ ቆይተዋል። በምርጫ ሊገኝ የሚችል አንዳች ውጤት እንደሌለ ይናገራሉ። በቅርቡ አቶ ሀብታሙ አሰፋ የሚባሉ ሰው ”እነ አቶ መለስ ማጅራቱን ከመቱት ምርጫ ተቃዋሚዎች ለምን እራሳቸውን አያገሉም? … ትግሉ የሀገሪቷን ዴሞክራሲያዊ ሂደት ለማጎልበትና ህዝቡን አታግሎ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት ሥርዓት ለመገንባት ከሆነ በዚህ ምርጫ መሳተፍ ከዚህ ግብ አያደርስም” ሲሉ በምርጫው መሳተፍ ለትግሉ ጥቅም እንደማያመጣ ይናገራሉ። ("እነ አቶ መለስ ማጅራቱን ከመቱት ምርጫ ተቃዋሚዎች ለምን እራሳቸውን አያገሉም?" የሚለውን የአቶ ሀብታሙ አሰፋን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

 

ፕሮፌሠር መስፍን ወልደማሪያም የሚመሩት ሰሞኑን አንዳንድ ድምጾች እያሰማ ያለው የዝም አንልሞች ቡድን ደግሞ ”እንዴት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታስራ ምርጫ ይገባል?” በማለት በመድረኩ ላይ ጠንካራ ትችት እያቀረበ ነው።

 

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የማንንም አስተያየት ለማጣጣል አይደለም። ነገር ግን ከስሜት በፀዳ መልኩ ሁኔታዎችን ከሁሉም አቅጣጫዎች ማየት እንድንችልና በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት፣ ቢቻል ሁላችንንም ወደ አንድ አቅጣጫ ሊያመጣ ውይይት እንድናደርግ ነው።

 

በተቃዋሚ ወገን ያለን ሁላችንም የምንስማማበትና ክርክር የማያስፈልግው አንድ ነጥብ አለ። ይህም የ2002 ዓ.ም. ምርጫ፣ በምንም መስፈርትና ሚዛን ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሊባል አይችልም። የጠቅላላው ምርጫ ሂደት፣ ቅድመ ምርጫን፣ የምርጫ ወቅትንና ድህረ ምርጫን ያካትታል። ”አንድ ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ወይም አይደለም” ብሎ ለመፍረድ፣ ምርጫ እስኪደረግ የግድ መጠበቅ የለበት። ከምርጫ በፊት ያሉትን ሁኔታዎች በማጥናት የምርጫውን ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊነት ከወዲሁ ማረጋገጥ ይቻላል።

 

የቅድመ ምርጫ ወቅት ላይ በማተኮር አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታዎች ለመቃኘት እንሞክራለን።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ የቅንጅት ወራሽ የሆነውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኘው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ነው። በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የአንድነት ፓርቲ ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ መምጣት ሲጀምር፣ ገዢው ፓርቲ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የድርጅቱን ሊቀመንበር በግፍና በጭካኔ አሰረ።

 

ሌላው ቢቀር የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ብቻ ምርጫውን ኢፍትሃዊና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ያደርገዋል። ህዝብን አስተባብራ በዝረራ ልታሸንፍ የምትችለውን ታላቅ ኢትዮጵያዊት፣ በድምፅና በሃሳብ ክርክር እንደማያሸንፏት ሲያውቁ፤ እነ አቶ መለስ ዜናዊ በጉልበት እርሷን አሳስረው ”ምርጫ አሸነፍን” ቢሉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይስቅባቸዋል እንጂ በህዝብ እንደተመረጡ አድርጎ የሚቆጥር አይኖርም።

 

ይህ ብቻ አይደለም። በዚህ ሁለት ሣምንታት ብቻ ሁለት ጠንካራ የመድረኩ አባላት፣ ርህራሄ በሌለበት ሁኔታ ተደብድበው ተገድለዋል። የመጀመሪያው አረጋዊ ገብረ ዮሐንስ ይባላል። በትግራይ መድረኩን ወክሎ ለተወካዮች ምክር ቤት ሊወዳደር የቀረበ ወንድማችን ነበር። ሁለተኛው ደግሞ ወጣት ቢያንሳ ዳባ ይባላል። በአምቦ አካባቢ የመድረኩ አደራጅ ነበር። አንድ ማታ የህወሓት/ኢህአዴግ ደህንነት አባላት ወደ ቤቱ መጥተው ደበደቡት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ከድብደባው ማገገም ስላልቻለ ሕይወቱ አለፈች። እነዚህ ስማቸው የታወቁ ናቸው እንጂ በየቦታውና በየወረዳው መድረኩን ወክለው የሚወዳደሩ፣ መድረኩን የሚደግፉ የተገደሉ፣ ከሥራ የተባረሩ፣ የታሰሩ፣ ወከባና ዛቻ የሚደርስባቸው ጥቂት አይደሉም። ህዝቡ ኢህአዴግን ካልመረጠ ችግር እንደሚያጋጥመው ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ነው። ኢህአዴግን እንደሚመርጡ ዜጎች በመሃላ እንዲፈርሙ እየተደረገ ነው። ይህ ሁሉ ምን ያህል ምርጫው ቀልድና ጨዋታ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

 

እቀጥላለሁ። ወደ አርባ ሰባት ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ምርጫውን የሚታዘቡ፣ ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚከፈላቸው የህወሓት/ኢህአዴግን አሸናፊነት የሚያረጋግጡ ታዛቢዎች ተዘጋጅተዋል። እነዚህ ታዛቢዎች የኢህአዴግ ሰዎች ናቸው ብንል አንሳሳትም። የምርጫውን ውጤት የሚወስነው ደግሞ ድምፅ ሰጪው ሳይሆን ድምፅ ቆጣሪው ነው። ቆጣሪው ኢህአዴግ በሆነበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ በምንም መስፈርት ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችለም።

 

ይህ የ2002 ምርጫ በምንም ተዓምር ኢፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሊባል እንደማይችል ሌላም ሌላም የተጨበጡና የማያከራክሩ መረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል። ከላይ እንደተገለጸው ብዙም በተቃዋሚው ወገን ዘንድ የሚያከራክር ነገር አይደለም።

 

ክርክሩና አለመስማማቱ የሚመጣው ”ምርጫው ከላይ እንደጠቀስኩት ኢ-ፍትሃዊን ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሆኖም፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በቀላሉ አጭበርብሮ ተመረጥኩኝ ብሎ የሚያውጅበት ሁኔታ ሰፊ ቢሆንም፤ ከምርጫው እራሳችንን ማግለል ነው የሚበጀው ወይንስ በምርጫው ገፍቶ መሄድ?” በሚለው ላይ ነው።

 

ምርጫውን አለመሳተፍ ከሚያመጣው ጥቅም ይልቅ ብዙ ጉዳት እንደሚኖረው በማሳየት ከአንዳንዶች ዘንድ የምንሰማው የምርጫ ቦይኮት ዘመቻ ከንዴትና ከስሜት የመነጨ እንጂ ጥቅሙንና ጉዳቱን ያመዛዘነ እንዳልሆነ ለማብራራት እሞክራለሁ።

 

ከምርጫው ተቃዋሚዎች እራሳቸውን ቢያገሉና ኢህአዴግ አሸንፌያለሁ ብሎ ቢያወጅ፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና አንዳንድ የውጭ ሜዲያ ጋዜጠኞች ለጥቂት ቀናት ያወግዙ ይሆናል። ነገር ግን ገንዘቡ በእጃቸው የሆነ የምዕራባውያን ሀገሮች አቶ መለስን ማቀፋቸው አይቀርም። በምንም መልኩ ምርጫ ተጭበረበረ ብለው አሁን ያለውን አገዛዝ ከመደገፍ ወደ ኋላ አይሉም። ለእነርሱ ግድ የሚሰጣቸው የዴሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን የመረጋጋት ጥያቄ ነው። ኢህአዴግ ደግሞ በሶማሊያ፣ በሱዳን ፣ በኤርትራ ካሉ ገዢዎች ጋር ሲነጻጸር፣ ለምዕራባውያኑ የተሻለ መንግሥት ነው። ስለዚህም ”አገዛዙ ተቀባይነት እንዳያጣ አስደርገዋለሁ” ብሎ መድረኩ ከምርጫው ቢወጣ የሚያገኘው አንዳች ፋይዳና ጥቅም አይኖርም። በመሆኑም መድረኩ ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። አንድ በሉ።

 

በምርጫው የሚሳተፉ እንደ ኢዴፓ፣ መኢአድ ያሉ ድርጅቶች አሉ። መኢአድና ኢዴፓ በርካታ ወረዳዎች ተወዳዳሪዎች አሰልፈዋል። ስለዚህ ቦይኮቱ ሁሉንም ድርጅቶች ያቀፈ ሊሆን አይችልም። መድረኩ ብቻውን ቦይኮት ቢያደርግ አቶ መለስ ከኢንጂነር ኃይሉ ሻውልና ከአቶ ልደቱ ጋር በሸራተን እንደተጨባበጡት፤ መድረኩ ወደ ጎን ተደርጎ፣ ከኢዴፓና ከመኢአድ ጋር በመሆን፣ በኢትዮጵያ ምድበለ-ፓርቲ እንዳለ መለፈፍ ይችላሉ። በሌላ አባባል ኢህአዴግን የሚያጅቡ ሌሎች ይኖራሉ ማለት ነው። ስለዚህ ሁኔታው መድረኩን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ስለሆነ መድረኩ በምርጫው መሳተፍ አለበት። ሁለት በሉ።

 

የምርጫ ቦይኮት ድርጅታዊ ሥራ ይጠይቃል። ህዝብን እስከ ታች ድረስ ማንቀሳቀስ፣ ለመምረጥ እንዳይሄድ በየቦታው በግልጽ ይሁን በኅብዕ ቅስቀሳ መደረግ አለበት። የደቡብ አፍሪካ ኤኤንሲ በየቦታው፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየትምህርት ቤቱ መረብ ነበረው። አንድ ህዝባዊ ጥሪ በተደረገ ጊዜ ህዝቡ በቀላሉ ተግባራዊ ያደርገው ነበር። የቦይኮት ዘመቻዎችም ገዢው የአፓርታይድ አገዛዝ ያስጨንቁ ነበር።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ በየክልሉ በየወረዳው ህዝብን ያደራጀና ጠንካራ መረብ የዘረጋ ድርጅት የለም። መድረኩ ያንን ለማድረግ እየሞከረ ነው። ግን ሀገር አቀፍ ጥሪ አቅርቦ፣ ጥሪው በህዝብ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ህዝባዊ ንቅናቄ ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመዘርጋት ይችል ዘንድ ድርጅታዊ ብቃት ገና የለውም። ይህ ብቃት ሳይኖር ገዢውን ፓርቲ ፊት ለፊት መጋፈጥ ቅንጅት በ97 የሠራውን ስህተት መድገም ነው። (ቅንጅት በ97 አንጋፋ መሪዎቹ የነበሩት አቶ ልደቱ፣ ኢንጂነር ኃያሉ ሻውል፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ፕሮፌሠር መስፍን፣ … በጥንቃቄና በትህትና፣ በመግባባትና የሀገርን ጥቅም በማስቀደም የድርጅቱን አንድነት ጠብቀው፣ ትግሉን ቀጥለው ቢሆን ኖሮ፣ አገዛዙን ማንበርከክ የሚችል ብቃት ያለው ድርጅት ይሄን ጊዜ ይኖር ነበር)። ህዝባዊ አቅም ሳይገነቡ ከአምባገነኖች ጋር ፊት ለፊት የሚገጥሙ የፖለቲካ ድርጅቶች በስሜት የሚመሩ፣ የትም የማይደርሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። መድረኩ እንደነዚህ አይነት ድርጅት ሊሆን አይገባም። ማስተዋል ያለውና የበሰለ ውሳኔ በመውሰድ መድረኩ ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ሦስት በሉ።

 

መድረኩ እራሱን ከምርጫው ቢያገል አገዛዙ ”ፀረ-ሠላምና ሽብርተኛ ናቸው” በማለት የመድረክ አባል ድርጅቶችን ሕጋዊነት ሊነጥቅ እንደሚችል መቼም መገመት አይከብድም። ሕጋዊነት ከሌለ ደግሞ በግልጽ ሀገሪቷ ውስጥ መንቀሳቀስ አይቻልም። ስብሰባዎች፣ ሠላማዊ ሰልፎች፣ ማናቸውም አይነት ዝግጅቶች በመድረኩ ሊዘጋጁ አይችሉም። የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጽ/ቤት ይዘጋል። አነሰም በዛም አሁን በሀገር ቤት እያየነው ያለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ይዳፈናል። ትግሉ የሚመራው አካል ያጣል። በሌላ አባባል አንድነት ፓርቲም ሆነ መድረክ የሚባል ነገር አይኖርም ማለት ነው።

 

መድረኩ ሲከስም ደግሞ መድረኩ እያደረገ ያለውን ትግል ተክቶ ህዝቡን የሚያደራጅና የሚመራ አካል በቀላሉ ከወዴት ሊመጣ ይችላል? በውጭ ሀገር ያሉ ድርጅቶች ህዝቡን የማደራጀት ኃላፊነት ሊወስዱ ይችላሉን? አይችሉም። ይኸው ለ19 ዓመታት አላየንም። በመሆኑም መድረኩ ከምርጫው በመውጣት በሕልውናው ላይ አደጋ መጣል ስለሌለበት ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። አራት በሉ።

 

መድረኩ በምርጫ ሂደት መሳተፉ በራሱ ያመጣቸው ውጤቶች አሉ። በየክልሎቹ እየሄደ ህዝብን በማደራጀት ላይ ይገኛል። ህዝብ ለመብቱና ለነፃነቱ እንዲታገል፤ ከፍርሃት እንዲላቀቀ፣ በራሱ እንዲተማመን፣ ቀንበርና ግፍን በቃኝ እንዲል ቅስቀሳ እየተደረገ ነው። ይህ መድረኩ ከምርጫው በፊት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ምርጫውም ካለቀ በኋላ እንዲቀጥሉ መደረግ አለበት። ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ ነው ህዝብ ተደራጅቶ አገዛዙን መጋፈጥ የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር የሚችለው። በፊታችን የሚደረገውን ምርጫ ኢህአዴግ አሸነፈ ማለት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይገዛል ማለት አይደለም። ህዝብ የማደራጀት ሥራ በሚገባ ከተሠራ የሥርዓት ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማምጣት ይቻላል። ነገር ግን ህዝብን የሚያደራጅ አካል ከሌለ የዛሬ አምስት ዓመት ብቻ አይደለም፤ ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት ኢህአዴግ መግዛቱ አይቀርም። በመሆኑም መድረኩ ሕጋዊነቱን እንደያዘ ቁልፍ የሆነው ህዝብን የማደራጀት ሥራ ይሠራ ዘንድ የግድ በመሆኑ፣ መድረኩ ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። አምስት በሉ።

 

መድረኩ ከምርጫው እራሱን ቢያገል ኢህአዴግ ”አጭበረበረ” ማለት አይቻልም። በፎርፌ አሸንፏል። አጭበረበረ ማለት የሚቻለው በምርጫው ተሳትፎ በርግጥ መስረቁን በማጋለጥ ነው። ምርጫው ከተደረገ በኋላ፣ ምርጫው እንደተሰረቀ መግለጫ በማውጣት የምርጫውን ውጤት ማጣጣል ይቻላል። ከላይ እንደጠቀስኩት የዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ብዙ ለዲሞክራሲ ጉዳይ ቦታ አይሰጥም። ለውይይት ያህል ግን፣ ግድ ይሰጣል ብለን ብንቀበል እንኳን፤ ገዢውን ፓርቲ ማሳጣት የሚቻለው በምርጫው ባለመሳተፍ ሳይሆን ተሳታፊ ሆኖ ምርጫ መጭበረበሩን በማሳየት ነው። በመሆኑም መድረኩ ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ስድስት በሉ።

 

”ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ታስራ እንዴት መድረኩ ምርጫ ይገባል” የሚሉ ወገኖች አሉ። በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ብቸኛ ድርጅት የአንድነት ፓርቲ ነው። የአንድነት ፓርቲ በሚያደርጋችው ህዝባዊ ስብሰባዎች ሁሉ የብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ሕገ-ወጥ እንደሆነ በመቀስቀስ፣ ህዝቡ እንድትፈታ እንዲታገል ግፊት እያደረገ ነው። በመስቀል አደባባይ የተጠራው ሠላማዊ ሰልፍ ቢከለከልም፣ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ የአንድነት አባላት የእርሷን ጉዳይ ከማንሳትና ለእርሷም ከመሟገት የቦዘኑበት ጊዜ የለም። በቴሌቭዥን በሚደረጉ ክርክሮች የብርቱካን ጉዳይ ይነሳል። የአንድነት ፓርቲ ወጣቶች የብርቱካን ኬኔተራን እየለበሱ ከኔቴራውን በመሸጥ ታስረዋል። ለብርቱካን የሻማ ማብራት ዝግጅት ላይ ለመካፈል ሁለት ቀናት ሙሉ በእግር ተጉዘው የሚመጡ ኢትዮጵያውያን አሉ። ትላንት ”ስለብርቱካን ምንም አይባልም” እያሉ ሲከሱ የነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ ”የርሷን ስም አሥር ጊዜ እያነሱ መጠቀሚያ እያደረጓት ነው” እስኪሉ ድረስ የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም መድረኩ የብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ዋና አጀንዳው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው።

 

መድረኩ ከምርጫው እራሱን ቢያገል በምን ሂሳብ ነው ብርቱካን ሚደቅሳ ልትጠቀም የምትችለው? ይልቅስ አንድነት/መድረኩ ሕልውናውን ቢያጣ በሀገር ውስጥ የብርቱካን አድቮኬት (ተቆርቋሪ) ሊሆን የሚችል ማን አለ? የትኛው አካል ነው በርሷ ጉዳይ ከፈረንጆች ጋር በሀገር ቤት የሚነጋገረው? ማነው በርሷ ጉዳይ ህዝብን የሚቀሰቅሰው? ማን ነው፣ ሀገር ውስጥ ካሉት፣ የብርቱካንን በግፍ መታሰር የዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርገው? በእውኑ እንነጋገርና የመድረክና የአንድነት መኖር ነው ወይስ መጥፋት ለብርቱካን መፈታት የሚጠቅመው?

 

ነገሮችን ከሁሉም አቅጣጫ ለምንመለከት መልሱ ቀላል ይመስለኛል። በመሆኑም ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳትረሳ፣ በሀገር ውስጥ የብርቱካን ትፈታ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር መድረኩ መኖር አለበት። በመሆኑም መድረኩ ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ሰባት በሉ።

 

ብዙዎቻችን ምርጫውን እንደቀልድና ጨዋታ ብንወስደውም ህዝቡ ውስጥ የታመቀው የነፃነት እሳት ተዓምር ሊፈጠር እንደሚችልም መዘንጋት የለብንም። በአንዳንድ የደቡብ ክልሎች በምርጫ ዘጠና ሰባት እንደታየው፣ ህዝቡ በየወረዳው በራሱ አነሳሽነት ተነሳስቶ በፊቱ ድምፁ እንዲቆጠር ሊያስገድድ ይችላል። ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ ምን ያህል የሰፋ እንደሚሆን ለማወቅና ለመተንበይ ይከብዳል። ቢሆንም የህዝብ ተዓምር የመሥራት ዕድልንም ስለሚከፍት መድረኩ በምርጫው ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ስምንት በሉ።

 

ውድ ኢትዮጵያውያን! አንዳንዶቻችን ትግሉን ከምርጫ ጋር ብቻ እናገናኘዋለን። ትግሉ ከዚያ ያለፈ ነው። አንዳንዶቻችን ትግሉ የግለሰቦች ጉዳይ ብቻ እናደርገዋለን። ትግሉ ከግለሰቦች ጉዳይ ያለፈ ነው። ትግሉ የኢትዮጵያ ህዝብ መብቱና ነፃነቱ ተከበሮ፤ የሀገሩ ባለቤት ሆኖ፣ የሚኖርበትን ሥርዓት ለመገንባት ነው። ይህ አይነቱ የነፃነትና የመብት ጥያቄ ደግሞ እስካልተመለሰ ድረስ ትግል አይቆምም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳለችው ”ሰው ያለ ነፃነቱ ምንድን ነው?”

 

አንድ ተብሎ በመቁጠር ነው ወደ ሁለት የሚኬደው። እየወደቁ፣ እየዛሉ ነው ወደፊት የሚገሰገሰው። የሀገራችን ጉዳይ ጨዋታ አይደለም። የሀገራችን ጉዳይ በግለሰቦች በማዘናችን የምንተወው አይደለም። የሀገራችን ጉዳይ የሕልውናችንና የማንነታችን ጉዳይ ነው።

 

መድረኩ ከምርጫው እራሱን እንዲያገል ጥሪ እያቀረቡና ግፊት እያደረጉ ያሉ ወገኖች በርግጥ ያሉትን ሁኔታዎች በሙሉ በጥሬው ካገናዘቡ ሃሳባቸውን ይቀይራሉ የሚል እምነት አለኝ።

 

አይ አሁንም ”በምርጫው መሳተፍ አይገባም” የሚል አቋም የሚይዙ ወገኖች ካሉ ደግሞ፤ የመከራከሪያ ነጥባቸውን ለመስማት ዝግጁዎች ነን። አንድ ሁለት ብለው የምርጫውን ቦይኮት ጥቅም ያስረዱን። ያላቸውን አማራጮች ያቅርቡልን። መከሰስ፣ መተቸት፣ መሳደብ በጣም ቀላል ነው። መፍትሔ ማምጣት ግን ፍፁም የተለየ ነገር ነው። ሌሎች ድርጅቶች የሚሠሩትን ማጣጣል አንድ ነገር ነው። ሠርቶ ማሳየት ግን ሌላ ነገር ነው።

 

እዚህ ላይ አቆማለሁ። ለሁላችንም ቸር ይግጠመን!


ግርማ ካሣ

( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ሚያዝያ 24 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ