በቀልድ ምርጫ መሳተፍ ትርጉሙ ምንድነው?
ይልማ በቀለ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ውድ ወንድሜ አቶ ግርማ ካሣ ያቀረቡትን ጽሑፍ በአዲስ ቮይስ ድረ ገጽ ላይ አንብቤዋለሁ። አቶ ግርማ ካሣ በየጊዜው በዳያስፖራ ድረ ገፆች ላይ በአለው የሀገራችን ሁኔታ የሚጽፉትን ተከታትዬ አነበዋለሁ። ጊዜዎትን ወስደው፤ በጥሞና አስበው የሚያወጡት ጽሑፍ አንባቢዎች ስለ ውድ ሀገራችን እንድናስብ ያበረታታናል ብዬ አምናለሁ።
ዛሬ ግን እኔ ማተኮር የፈለግሁት ሰሞኑን በጻፉት “የፊታችን ምርጫ ቀልድ ነው - መድረኩ ግን መሳተፍ ይበጀዋል” በተባለው ላይ ነው። (የአቶ ግርማን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
ጽሑፉን የሚጀምሩት ”... ህወሓት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማድረግ ይዘጋጃል ታዛቢዎች አዲስ አበባ ገብተዋል፣ መድረክ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ... የምርጫ ዘመቻው አጧጥፈውታል ...” ብለው ነው። አስደሳች ጉዳይ ነው።
ስለ ዳያስፖራው ደግሞ ሲናገሩ ግንቦት ሰባትና አንዳንድ ተቃዋሚዎች ”ምርጫውን ህወሓት ስላሸነፈው ’ያለመሳተፍና እራስን ማግለል’ የሚል የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፍተዋል” ይላሉ። እነፕሮፈሠር መስፍንና ደጋፊዎቻቸው ደግሞ እንዴት ወ/ት (ሊቀመንበር) ብርቱካን ታስራ ምርጫ ይገባል የማለት ጥያቄ እያነሱ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
አቶ ግርማ ካሣ፤ የጽሑፋቸውም ዓላማ ውይይት ለማምጣት መሆኑን ይገልጹና መደምደሚያው ላይ ”... ‘በምርጫው መሳተፍ አይገባም’ የሚል አቋም የሚይዙ ወገኖች ካሉ ደግሞ የመከራከሪያ ነጥባቸውን ለመስማት ዝግጁዎች ነን። አንድ ሁለት ብለው የምርጫውን ቦይኮት ጥቅም ያስረዱን። ያላቸውን አማራጮች ያቅርቡልን። መክሰስ፣ መተቸት፣ መሳደብ በጣም ቀላል ነው። መፍትሔ ማምጣት ግን ፍፁም የተለየ ነገር ነው። ሌሎች ድርጅቶች የሚሠሩትን ማጣጣል አንድ ነገር ነው። ሠርቶ ማሳየት ግን ሌላ ነገር ነው” ብለው ኃይል በተሞላው ግሳፄ ይዘጋሉ።
በጣም ጥሩ አቶ ግርማ! ... እኔም በበኩሌ በጣም እስማማለሁ። በኔ አስተሳስብ ይሄ ጽሑፍ ለመጀመሪያ ግዜ የመድረኩን ዓላማ ከማድበስበስ አልፎ በግልጽ ያወጣ ነው ብዬ አምናለሁ። መድረኩ ምን ይፈልጋል የሚለውን ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመልስ ይመስላል። ባይመልስም ይሞክራል።
ወደ ዋናው ቁም ነገሩ እንሂድና፤ ጽሑፉ የህወሓትን መንግሥት ተቋሚዎች በሙሉ የምንስማማባቸውን ነጥቦች ሲያቀርብ ዋና ብሎ የሚያስማማንም በቀይ ያስምረዋል ‘የ2002 ምርጫን ከምንም መሳፍርት ሚዛን ፍትሓዊና ዲሞክራሲያዊ ሊባል አይችልም’፤ ክዚህም አልፎ ያለውን ችግር ሲያብራሩ የወ/ት (ሊቀመንበር) ብርቱካን ያለ አግባብ መታስር፤ በግልፅ የምናውቀው ሁለት ዕጩዎች መገደል፣ በምርጫው ምክንያት የብዙ ወገኖች መጎሳቆልና የመንግሥት ሠራተኞች በማስገደድ የመሃላ ፊርማ መደረጉን ገልፆ ‘ይህ ሁሉ ምን ያህል ምርጫው ጨዋታ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው’ ይላል።
ትንተናውን በመቀጠልም ህወሓት እስክ አርባ ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች በታዛቢነት የሚያገለግሉ አባሎቹን (ካድሬ) መልምሏል፤ ማለትም ይላሉ አቶ ግርማ፤ ‘የምርጫውን ውጤት የሚወስነው ደግሞ ድምፅ ሰጪው ሳይሆን ድምፅ ቆጣሪው ነው’ ቢባል ህወሓት የሚያደርገው ምርጫ በምንም መስፈርት ነፃናዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም ብሎ በሩን ይቀረቅራል።
ውድ አንባቢ ሆይ! ታዲያስ ክርክሩ ምን ላይ ነው ብለው ትንሽ ቢቸገሩ አያስደንቅም። ምክንያቱም በፀሐፊው አነጋገር ህወሓት ወይም የአቶ መለስ ድርጅት የዋናው ተቃራኒ ፓርቲ ሊቀመንበርን በግፍ አስሮ፤ የፓርላማ ዕጩዎችን ገድሎ፣ ከሚኖሩበት አፈናቅሎ፣ ሥልጣኑን በመጠቀም ሠራተኞችን የባርነት ቃል ኪዳን አስፈርሞና ካድሬዎቹን የምርጫ ታዛቢ ብሎ ሹሞ፤ ለይስሙላና ፈረንጆችን ለመደለል በሚያደረገው ምርጫ ላይ መሳተፍ ተገቢ ነው ብለው ክርክራቸውን ያቀርባሉ። ስምንት ነጥቦችም ያስቀምጣሉ።
‘ክርክሩና አለመስምማማቱ የሚመጣው’ ይላሉ ፀሐፊው ‘ምርጫው ... ኢፍትሃዊና ኢ-ዲሞክራሲያ ሆኖም፣ ህወሓት/ኢህአዲግ በቀላሉ አጭበርብሮ ተመረጥኩኝ ብሎ የሚያውጅበት ሁኔታ ሠፊ ቢሆንም፣ ከምርጫው እራሳቸንን ማግለል ነው የሚበጀው ወይንስ በምርጫው ገፍቶ መሄድ? በሚለው ላይ ነው።
ፀሐፊው የሚሉን በምንም አይነት መንገድ የአቶ መለስ መንግሥት የመሸነፍ ሃሳብ የለውም፣ መሬትና ሰማይ ቢገናኝ አይሸነፍም፤ ግን ቢሆንም ምን አለበት ገብተን ብንሸነፍ ነው። አቶ መለስ ‘ዓይናችሁን ጨፍኑ ላታልላችሁ እፈልጋለሁ’ ሲሉ ኩታ ማቀበል እንዴት መልካም ይሆናል ውድ ወዳጄ?!
ግድ የለም እሺ ብለን እስቲ ፀሐፊው የዘረዘሩትን ስምንት ንጥቦች እንመልከታቸው። በመጀመሪያ የወያኔው መንግሥት ከምርጫው ማግስት አሽነፍኩ ብሎ ሲያውጅ፣ ይላሉ ፀሐፊው፣ የምዕራብ መንግሥታትና ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጥቂት ያወግዙና ይቀበሉታል፤ ስለዚህ ‘መድረኩ ከምርጫው ቢወጣ የሚያገኘው አንዳች ፋይዳና ጥቅም አይኖርም’። ትንሽ ግራ የሚያጋባ አነጋገር ነው። ምርጫው የሚካሄደው በኢትዮጵያኖች ለኢትዮጵያን ከሆነ የፈረንጆች መቀበልና አለመቀበል በዚህ ውስጥ ምን አገባው። በህወሓት መንግሥትን ሕገ-ወጥ አገዛዝ እሳት የሚነደው ኢትዮጵያዊ ነው ወይስ ፈረንጅ? ታድያ መድረኩ መጨነቅ ያለበት ስለ ህዝቡ ወይስ ስለራሱ? ትላንት ኬንያ ውስጥ የተጭበረበረ ምርጫ ሲካሄድ ፈረንጆቹ’ኮ ተቀብለውት ህዝቡ ነው እኮ አይሆንም ያለው። እስቲ በታሪክ ተበዳዩ ሳይጮህ ዳኝነት የተጠራበት ጊዜ ወይንም ቦታ ይነገረን?
በሁለተኛ ደረጃ ህወሓት መኢአድንና፣ ኢዴፓን የመሳሰሉ ምርኮኞች ስላሉት መድረኩ ብቻውን ይቀራል ስለዚህ መሳተፉ ይበጃል ነው። በጣም ደካማ ክርክር ይመስላል። ለመሆኑ ህወሓት መቼ አጃቢ አጥትቶ ያውቃል? ጥያቄው አጃቢነት ለማን ጠቀመ ቢሆን ጥሩ ይመስላል። አልበቃ ተብሎ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ትግል ይጠቀሳል። ታድያ እኮ እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ ስቲቭን ቢኮ ያስተማሩን ሌላ ነው። በሠላም ይመረጣል ካልሆነም በሰደፍ እንጅ ኩታ አቀብሉኝ ዓይኔን ልሸፍን አልወጣቸውም።
በአራተኛ ደረጃ መድረኩ እራሱን ቢያገል አገዛዙ ፀረ-ሠላምና ሽብርተኛ በማለት ሕጋዊነቱን ይነጥቀዋል ስለዚህ በግልጽ መንቀሳቀስ፣ ስብሰባዎች ሠላማዊ ሠልፎች ማናቸውንም ዝግጅት ማድረግ አይችልም፣ ጽ/ቤቱም ይዘጋል ይላሉ። ችግሩ የሕገ-ወጥ መንግሥትን ባህሪን ካለመገንዘብ የመጣ ይመስላል። የፓርቲው ሕጋዊነት እኮ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተመሰረተ ነው እንጅ፤ በገዥው በጎ ፈቃድ የተሰጠ አይደለም። ስለዚህ የመድረኩ ሥራ ገዥው የራሱን ሕግ እንዲያከብር ማስገደድ ነው እንጂ እንደ ቄጠማ መሽመድመድ መሆን የለበትም። እውነቱ ግን መድረኩ ዛሬ ሕጋዊ ሆኖ ከላይ የተጠቀሱትን መች አደረገና? ለሊቀመንበርዋ አንድ ዓመት እስራት የሻማ ማብራት ዝግጅት ዝግ ቤት ውስጥ የተደረገው በሕገመንግሥቱ የተፈቀደውን ለማስከበር ወደ ኋላ ስለተባለ አይደለም? በተራ ካድሬ ስብሰባ የሚከለከለው፣ ሽማግሌ አሮጊት የሚደበደበው ሐቅ ነው’ኮ።
አምስተኛው ነጥብ ለቁጥር የገባ ይመስላለ። መድረኩ አሁን ‘የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ምርጫውም ካለቀ በኋላ እንዲቀጥሉ መደረግ አለበት’ ይላል። ችግሩ ግን አሁን በምርጫ ሰበብ ፈረንጆቹ ባሉበት እንኳን ያለ ህወሓት ፈቃድ መሰባሰብ ያልቻለ ታዲያስ ከምርጫው በኋላ የሚሆን ይመስላል? ታዛቢ ይፍረድ። ‘ኢህአዲግ አሸነፈ ማለት ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይገዛል ማለት አይደለም’ ሲሉ ምን ማለታችው ይሆን?
ስድስተኛው ስለ ፈረንጆች መቀበል አለመቀበል ስለሆነ መጀመሪያው ላይ ያየነው መሰለኝ። ሰባተኛው ነጥብ በእውነት ላይ የተመረኮዘ አይመስልም። በመላው ጽሑፉ ሊቀመንበር ብርቱካን የምትጠራው ወ/ት ብርቱካን ተብላ መሆኑ ምክንያቱ አልገባኝም። ሆኖም መድረኩም ቢሆን አንድነት የሊቀመንበሯ አንደኛ ተሟጋች ናቸው ማለት እውነትን እንደማጣመም ይቆጠራል። በቅርብ ጊዜ እንኳ ሕመሟን ለዓለም ያስታወቁት ወዳጆቿ ናችው እንጂ ጓዶችዋ ነን ባይዎች አይደሉም። በዳያስፖራውም የሊቀመንበሯን ጉዳይ በትጋትና ባለመሰልቸት የሚያካሂዱት በፈቃደኝነት የተቋቋሙት ድርጅቶች ናቸው እንጂ በሰሜን አሜሪካ ያለው የአንድነት ደጋፊ ቡድን አይደለም።
በስምንተኛ ቁጥር ላይ በተጠቀሰው አስተሳሰብ መስጠት ትንሽ ይቸግራል። እኔ እንደማውቀው ጌታ እግዚአብሔር ያለው እኔም እንድረዳችሁ መጀመሪያ እራሳችሁን እርዱ መሰለኝ። ታድያ እጅ አጣምሮ ቁጭ ብሎ ‘ተዓምር’ መጠበቅ የት ያደርሳል? ማንም ኢትዮጵያዊ ይሄንን ምርጫ ፀሐፊው እንዳሉት ‘እንደ ቀልድና ጨዋታ’ አይወስደውም። በሌላ በኩል አቶ ግርማ “የፊታችን ምርጫ ቀልድ ነው” ብለው ሲተቹ ብዙዎቻችን የምንስማማ ነን ብዬ አምናለሁ። በርግጡ ደግሞ የአቶ መለስ መንግሥት ግን በህዝቡ ብሶት ላይ እየቀለደ መሆኑን የዓለም ህዝብ የሚያውቀው ይመስለኛል።
በኔ አስተሳሰብ ‘መድረክ’ በምርጫው ለመሳተፍ ሙሉ መብት አለው ብየ አምናለሁ። የመድረክ መሳተፍ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ካለበት መከራ የሚያወጣ መፍቻ ቁልፍ አለው ብየ አላምንም። የሀገራችን ሰው ሲተርት ‘የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያሰታወቃል’ ይላሉ። የመድረክም ጉዳይ እንደዛው ኹኖ አግኝቸዋለሁ። ባንድ በኩል ‘የሠላማዊ ትግል’ እያካሄድን ነው ይሉናል። ጠጋ ብሎ ሲታይ ግን ከመጽሐፉ አንድ ገጽ ብቻ ያነበቡ ይመስላሉ፣ ይኽውም ምርጫ ላይ ብቻ ያተኮረ ይመስላል። ታድያ እኮ ‘የሠላማዊ ትግል’ እነማሃታማ ጋንዲ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ኔልሰን ማንዴላ ያስተማሩን ልዩ ነው። እነሱ የተጠቀሙት እኮ ‘ካሮትና፣ ዱላ’ የተባለውን መንገድ መሰለኝ። መድረኩ ብዙ ካሮት የጫነ ይመስላል፤ ምናለ ዱላው ቢጠፋ አርጩሜ እንኳን ቢይዝ።
ሊቀመንበሯ ወንጀለኛ ነች፣ እሺ - ስብሰባ አይፈቀድም፣ እሺ - ተወዳዳሪዎች ይገደላሉ፣ እሺ - ... ወዘተ ... ወዘተ።
መቸስ አንድ ነገር ጥሩም ነው ወይም መጥፎ ለመባለ መሞከር አለበት። እነ አቶ መለስ ሥልጣን ከተፈናጠጡ ይኸው ወደ አሥራ ስምንት ዓመት ሆኖታል። አሁን የሚደረገው ምርጫ አራተኛው ይመስለኛል። የኔ ጥያቄ የተቃዋሚው ጎራ ነን እያሉ የአቶ መለስ ፓርላማ ውስጥ የተሳተፉ አንዳንድ አሉ፣ እስቲ እንደው ለእነዚህ አዛውንቶች ሥራ ከመስጠት በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ትርፍ አገኘ? እስቲ አሥራ ስምንት ዓመት አብሮ ከመሥራት ያመጡትን ጥቅም ይንገሩን? እስቲ ያሳለፉት አንድ ሕግ ካለ ይጥቀሱልን? በማንም ያልተመረጠ ካድሬ መጫወቻ ከመሆንና ለህወሓት ሌጅትሜሲ ከመስጠት በስተቀር ሌላ ምን የሚያሳዩት አለ?
ከራሳችንና ከዓለም ህዝቦች ታሪክ ብንማር የሚከፋ አይመስለኝም። ለምሳሌ ፋሺስት ጣልያን ውድ ሀገራችንን የደፈረ ጊዜ ቆይ እስቲ መጀመሪያ እንደራደርና ቀስ ብለን ሰጥ ብለን ተገዝተን እናስወጣዋለን አላልንም። አባቶታችን፣ እናቶታችን ጎበዝ ተነሳ ሀገርና ቤት ተደፍሮአል ነው ያሉት። አይ አሁን አቅም የለንም ቀስ ብለን እስከምንደራጅ መጠበቅ ይሻላል አልወጣቸውም። ለነፃነት ቀጠሮ አይያዝም። ነውር ነው።
ታዲያስ መድረኩ የሚለን ያለፈው አሥራ ስምንት ዓመት የተሞከረውንና ምንም ውጤት ያላመጣውን ለመሥራት ዕድል ስጡን ነው? ዛሬ በምርጫው ያላሳዩትን ኀሞት ነገ ደምወዝተኛና ባለሥልጣን ሲሆኑ ከየት ያመጡታል? የፈረንጆች አባባል ‘ምራ፣ ተከተል ወይም ከመንገዱ ውጣ’ የሚባለው እዚህ ቦታ ያለው አነጋገር መሰለኝ።
መደረኩን መልካም ዕድል እመኝለታለሁ። የመድረኩ መሪዎችን ቸሩ ፈጣሪያችን ይጠብቃቸው እላለሁ። ከህወሓት ጋር መደራደር የነብር ጭራ እንደ መያዝ ነው፣ መጨረሻው የሚያምር አይመስልም።
ይልማ በቀለ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



