እስክንድር ነጋ ታስረው ተፈቱ
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቤታቸው የፈረሰባቸው ድሆችን ሲጎበኙ ነበር
ኢዛ (ቅዳሜ ሚያዝያ ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 25, 2020)፦ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ዛሬ ጠዋት ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፓርቲው አመራሮች ገልጸዋል። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ተፈትተዋል።
አቶ እስክንድር በትክክል የታሰሩበትን ምክንያት ማወቅ ባይቻልም፤ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደነበር ተገልጿል። የአቶ እስክንድርን መታሰር በተመለከተ ከመንግሥት የተሠጠ ማብራሪያ ባይኖርም፤ ባልደራስ የሚጠቀምባቸው ማኅበራዊ ገጾች ላይም ሲነገር ነው የዋለው።
ከፓርቲው አመራሮች አንዱ የኾኑት አቶ ስንታየሁ ቸኮልም አቶ እስክንድርን በስልክ እንዳገኙ ገልጸዋል። አቶ እስክንድር የታሰሩበትን ቦታ ያመላከቱ ሲሆን፤ ለእስር ያበቃቸውን ምክንያት በስልክ እንደገለጹላቸው አቶ ስንታየሁ ተናግረዋ። ይህንንም “የባልደራስ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ በፖሊስ የታሰረበት ምክንያት፤ ኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 5 የድሆች ቤት መፍረስን አስምልክቶ፤ ለምን ተገኝተህ ድምፃቸውን ለሕዝብ ታደርሳለህ ብለው ገልጾልኛል” በማለት ገልጸዋል።
አንዳንድ ወገኖች ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ ከአራት ሰው በላይ ኾኖ መሰብሰብ ስለማይቻል፤ አቶ እስክንድር ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታስረው ይኾናል የሚል ግምት አላቸው። (ኢዛ)