ሀብታሙ አሰፋ

ምርጫ 2002 አስቀድሞ በሂደቱ ተጭበርብሮ የቀረው የመጨረሻ ቀን ቴአትር ብቻ ነው። የቴአትሩ አዘጋጆች እና መሪ ተዋንያኑ የእነ አቶ መለስ ቡድን ያሰበው እንዲሳካ መታጀብ ይፈልጋል። የዚህ የተጭበረበረ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን ላለፉት አምስት ዓመታት ሕገ ወጥ ሥራዎችን ሠርቷል። በዚህም ቀዳዳዎችን ሁሉ ደፍኜያለሁ ብሎ ይናገራል። ተደጋግሞ እንደተገለጸው የተደፈኑት ቀዳዳዎች የአፈና ሥርዓቱን በሥልጣን ለማቆየት የወጡ ሕገ ወጥ አዋጆችና ልዩ ልዩ እርምጃዎች ናቸው። አሸባሪው ”የፀረ-አሸባሪነት” አዋጅ ይቃወሙኛል ያላቸውን ሁሉ ለማፈን እየዋለ ነው። የፕሬስ ነፃነትን አደጋ ላይ ጥሏል። የአዲስ ነገር አዘጋጆችን መጨረሻ ልብ ይሏል። የነ ጄኔራል ተፈራ ማሞን የፈጠራ ክስ እና ሕገ ወጥ ውሳኔ ማንሳት ይበቃል። ምርጫውን በፈለገው መንገድ ለመቆጣጠር እንዲችል የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር የተቻለውን ሁሉ አድርጓል።

 

ዛሬ በመድረክ እና በጥቂት የአንዳንድ ተቃዋሚ አባላት ላይ አፈናው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ከተገደሉ፣ ከቆሰሉ፣ ከታሰሩ፣ ከተደበደቡ፣ ከሥራ ከተባረሩ አባሎች በተጨማሪ በቅርቡ በትግራይ በአንድ የመድረኩ አባል ቤት ቦንብ ጭምር ተጥሎ የሽብር ተግባር ተፈጽሟል። የአፈና ሥርዓቱ ሕገ ወጥ እርምጃ ግን በዚህ ብቻ አያበቃም። እነሱ ያሰቡትን ቴአትር በፈለጉት መንገድ ለማካሔድ እስካልቻሉ ድረስ ይሔ ሕገ ወጥ ተግባር ይቀጥላል።

 

የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የምንል ኢትዮጵያውያን ምርጫውን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ማንፀባረቅ ይስተዋላል። ለኔ ይሔ ጤነኛ ነው። አንዱ ወገን ምርጫው በግልጽ እንደሚታየው ከሂደቱ ጀምሮ አስቀድሞ የተጭበረበረ ነው። በምርጫ ዕለት ብቻ ዲሞክራሲያዊ አይሆንም። የዚህ የመጨረሻ ውጤት ለእነ አቶ መለስ ሕጋዊ ካባ ከማልበስ ውጭ ለህዝቡ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። የህዝቡን ጥያቄ ያነገቡና ለሕግ የበላይነት የቆሙ ተቃዋሚዎች የዚህ ሕገ ወጥ ሂደት ተሳታፊ መሆን የለባቸውም ረግጠው ሊወጡ ይገባል ይላል። መድረኩ ምርጫ ይግባ የሚለው ወገንም የምርጫውን አስቀድሞ መጭበርበርሩን ይቀበልና አለመሳተፉ ለመድረኩ ድርጅታዊ ህልውና ስለሚያሰጋው እስከመጨረሻው መሳተፍ ተገቢና ጠቃሚ ነው ብሎ ይከራከራል። ለኔ ይሔ ሁሉ ጤነኛ ነው። ፍርድ ሰጪው ነገሩን መዝኖ ለመወሰን አግጦ የወጣው ዕውነት ራሱ ስለሚናገር አይቸገርም።

 

በቅርቡ ”እነ አቶ መለስ ማጅራቱን ከመቱት ምርጫ ተቃዋሚዎች ለምን ራሳቸውን አያገሉም?” በሚል ለሰነዘርኩት አስተያየት ግርማ ካሣ የተባሉት ሰው ”የፊታችን ምርጫ ቀልድ ነው - መድረኩ ግን መሳተፍ ይበጀዋል!” በሚል ርዕስ ስምንት ነጥቦችን አንስተው ምላሽ ሰጥተዋል።

 

የጽሑፉን ይዘት አንስቼ እርስ በእርሱ የሚጋጩ ሃሳቦቻቸው ላይ የበኩሌን አስተያት ከመሰንዘሬ በፊት የሚቃወሟቸውን የገለጹበትን መንገድ አስመልክቶ ያነሱት ላይ አንድ ልበል። አስቀድሞ መጭበርበሩን ራሳቸው ከሚቀበሉት ምርጫ 2002 ተቃዋሚዎች ረግጠው መውጣት አለባቸው የሚሉት ላይ የሰነዘሩትን ስድብ ላንሳ። ሰው ከራሳችን የተለየ ሃሳብ ስላቀረበ መሰደብ አለበት ብዬ አላምንም። ተቃውሞዬን ከዚህ እጀምራለሁ።

 

በጽሑፋቸው ከሳቸው የተለየ ሃሳብ የሰነዘርነውን ”… ከአንዳንዶች ዘንድ የምንሰማው የምርጫ ቦይኮት ዘመቻ ከንዴትና ከስሜት የመነጨ እንጂ ጥቅሙንና ጉዳቱን ያመዛዘነ እንዳልሆነ ለማብራራት እሞክራለሁ …” ብለዋል። በሃሳብ መለየት መብት ነው። ይህን መብት ረግጠው ምርጫ አይግቡ የሚሉትን በስሜትና በንዴት የሚመሩ ሲሉ ምርጫ ይግቡ ባዮችን ደግሞ ጥቅምና ጉዳት አመዛዛኝ አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ። ፀሐፊው ለሃሳብ ልዩነት ከበሬታ ያላቸው አይመስልም። ዜጎች የተለየ ሃሳብ በማራመዳቸው ሊሰደቡ እንደማይገባ ይረዱታል ብዬ አምናለሁ። ፀሐፊው ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ብንሆን የአንድን ሰው ሃሳቡን መቃወም፣ መደገፍ ወይም የተለየ አስተያት መስጠት እንታገልለታለን የምንለው የዲሞክራሲያዊ መብት አንድ መገለጫ ነው።

 

እነ አቶ መለስ ተቃዋሚዎችን በክርክር መብለጥ ሲያቅታቸው አንዴ እንክርዳድ ሌላ ጊዜ አስራለሁ አሉ። አሰሩ ገደሉ። ማስፈራራታቸው፣ ዜጎች በሃሳብ ስለተለዩ የሚያዋርዱ፣ የሚንቁ፣ የሚያንቋሽሹ፣ በዚህ ሁሉ ማሸነፍ ሲያቅታቸው ወንጀል እየለጠፉ ንጹኀንን የሚገሉት አፋኞች ላይ የምንጠላውን ሥራ እኛው በተዘዋዋሪ መደገፍ እንዳይሆንብን መጠንቀቅ ይገባል። ራስንም ያስገምታል።

 

ፀሐፊው መድረኩ ቀልድ በሆነው ምርጫ መግባቱ ጠቃሚ ነው ብለዋል። እርስ በእርሱ የሚፋለስ መከራከሪያቸውንና በተያያዥ ያነሷቸውን ጉዳዮች ጠቃቅሼ የማልስማማባቸውን ነጥቦቼን አነሳለሁ።

 

ምርጫ አይግቡ የሚሉትን ሁሉ የመድረኩ እንቅስቃሴ ተቃዋሚዎች አድርገው ለማሳየት ሞክረዋል። የእነ ፕሮፌሠር መስፍን ምርጫ አይግቡ ጥያቄና የሌሎች ወገኖች ጥያቄ ከአንድነቱ ይልቅ ልዩነቱ ያመዝናል።

 

መድረኩን አልቃወምም። የመድረኩ እንቅስቃሴ ይቁም አልወጣኝም። በአደባባይ መድረኩን እቃወማለሁ ሲሉ የሰማኋቸው ለየበኩላቸው ፍላጎት እነ ፕሮፌሠር መስፍንንና መድረኩ ይጥፋ እያለ የተለያየ ጥላሸት ለመቀባት የሚሞክረውን የአቶ መለስ አስተዳደር ነው።

 

መድረኩን የምደግፈው ለህዝብ በገባው ቃል በሠላማዊ ትግል ታግሎ፣ ህዝቡን መርቶ የሕግ የበላይነት ለማስከበር እና ለህዝብ የሥልጣን ባለቤትነት እታገላለሁ ስላለ እንጂ፤ የየትኛውም የመድረኩ ድርጅቶች አባል አይደለሁም። እንደማንኛውም ዜጋ እታገልለታለሁ የሚለውን ዓላማ ግን እደግፋለሁ። ይህን ዓላማውን ለማሳካት አባላቶቹ እየተገደሉ፣ እየተደበደቡ፣ እየታሰሩና ዛሬም ልዩ ልዩ ጥቃት እየደረሰባቸው የሚሳተፍበት የምርጫ ሂደት በቅድመ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ መጭበርበሩን እያመነ ገብቶ የእነ አቶ መለስ ቴያትር አሳማሪ መሆኑ፤ እታገልለታለሁ ከሚለው ግብ አያደርስም፤ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም ብዬ ግን አምናለሁ። የመድረኩ መንገድ ብቻ ብቸኛ አማራጭ ነውም ብዬ አላምንም። ፀሐፊው ደግሞ የምርጫውን መጭበርበር ባይጠራጠሩም በዚህ ሂደት መድረኩ እንዲሳተፍ ይገፉታል።

 

”የምርጫውን ውጤት የሚወስነው ደግሞ ድምፅ ሰጪው ሳይሆን ድምፅ ቆጣሪው ነው። ቆጣሪው ኢህአዲግ በሆነበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ በምንም መስፈርት ነፃና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይቻልም።” ከላይ በጥቅስ ያሰፈርኩት የፀሐፊው ሃሳብ ነው። አስቀድመው ከዚህ ድምዳሜ የደረሱ ወገኖች ምርጫውን ተቃዋሚዎች በተለይም መድረኩ ረግጦ ይውጣ ሲሉ፤ እሳቸው የለም ምርጫ መግባት አለበት ሲሉ ያነሷቸውን ስምንት ነጥቦች በየተራ እንመልከታቸው።

 

”… አገዛዙ ተቀባይነት እንዳያጣ አደርገዋለሁ ብሎ ከምርጫ ቢወጣ የሚያገኘው ፋይዳና ጥቅም አይኖርም። በመሆኑም መድረኩ ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። አንድ በሉ።”

 

ፀሐፊው መድረኩ ምርጫውን ረግጦ ቢወጣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙኀን ካንድ ሰሞን ጫጫታ ያለፈ የሚያመጡት የለም ባይ ናቸው። ከዚህ ተነስተው መድረኩ በተጭበረበረው ምርጫ ይሳተፍ ብለዋል።

 

ከምርጫ 97 በፊትም እነ አቶ መለስ ሁለት የተጭበረበሩ ምርጫዎች አድርገዋል። በዚያ ሁሉ ሂደት ግን የምዕራቡን ዓለም ጠንካራ ተቃዋሚ የለንም ከማለት አልፈው፤ አመራራችን ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን የዜጎች እኩልነት የሰፈነበት ነው በሚል ዘረኛ ሥርዓታቸውንና እውነተኛ ማንነታቸውን በውሸት ካባ ሸፍነው ብዙዎችን ሲያሞኙ ነበር።

 

በምርጫ 97 ዛሬ ፀሐፊው የናቁዋቸው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን፣ የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች፣ የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች፣ የአውሮፓ ሕብረትና ሪፖርታቸው የዘገየው የካርተር ማዕከል ታዛቢዎች ጭምር የሥርዓቱን ምርጫ አጭበርባሪነት፣ የህዝቡን ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያለውን ቁርጠኝነት እና ለድምፁ ያለውን ከበሬታ፣ መብቱን ስለጠየቀ የተፈጸመበትን ግፍ በማጋለጥ፤ የነ አቶ መለስን እውነተኛ ማንነት በማጋለጥ ለሠሩት ወንጀል መቼም ቢሆን እንዲጠየቁ ትልቅ የማስረጃ ጉልበት ሰጥቷል። ምርጫውን ረግጦ መውጣት ጠቀሜታ የለውም የሚያሰኝ አይደለም።

 

ሌላው የአቶ መለስን አስተዳደር የምዕራባውያን መንግሥታት ትናንትም ሆነ ዛሬ ስለሚደግፉት ምርጫ መርገጥ ዋጋ የለውም መድረኩ ይሳተፍ ማለት ተቀባይነት የለውም። ምዕራባውያን የህዝቡን ጥንካሬ እና የራሳቸውንም ጥቅም የሚያዩ ስለሆኑ ዛሬ ወዳጅ ቢሆኑ ነገ ተመልሰው ያልተጠበቀ ውሳኔ ከመውሰድ አይመለሱም። ያንን ጥንካሬ ለማምጣት መድረኩ መሥራት አለበት እንጂ ገና ለገና ምዕራባውያን እነመለስን ከመደገፍ አይቆጠቡም ብሎ አርፋችሁ የተጭበረበረ ምርጫ አጃቢ ሁኑ ማለት ተስፋ ቆርጦ ተስፋ ማስቆረጥ ነው። የዛየር ህዝብ እምቢ ማለቱን እስኪያረጋግጡ ሠላሳ ዓመት ሙሉ ወዳጅ የነበሩትን የአምባገነኑን የሞቦቶ መንግሥት ፈጥነው ዞር በሉ ማለታቸውን ፀሐፊው የሚረሱት አይመስለኝም።

 

የፀሐፊው ሁለተኛ መከራከሪያ ነጥብ አስገራሚ ነው። መድረኩ ምርጫ መርገጥ የሌለበት ኢዴፓና መኢአድ በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ እንዳደረጉት በምርጫው ስለሚወዳደሩ መድረኩ ብቻውን አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል በሚል ነው።

 

መድረኩን እና ኢዴፓን በቀደመውም ጽሑፌ አላነጻጸርኩም። ምርጫውን ረግጠው ሊወጡ ይገባል የሚል ሃሳብ የሰነዘርኩት መድረኩና ህዝቡ እውነተኛ ተቃዋሚ ያላቸውን እንጂ አቶ ልደቱን አይደለም። አልሰሙ ካልሆነ ኢዴፓ ከወዲሁ ምርጫውን ተቃዋሚዎች እንሸነፋለን እያለ የነመለስን ሃሳብ በማጠናከር አጋርነቱን የበለጠ እያረጋገጠ ነው። ሁሉም ወገን የእያንዳንዱን የምርጫ ተወዳዳሪ ማንነት አጥርቶ ስለሚያውቅ መድረኩ ረግጦ ቢወጣ እንጂ ኢዴፓ ምርጫ ጥሎ ይውጣል የሚል ቅዠት የለውም።

 

ፀሐፊው ከዚህ ቀደም ስለ መድረኩ ጥንካሬ የተለያዩ ጽሑፎችን ጽፈዋል። ከዚህ አልፈው ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ብቸኛው መድኅን አስመስለው ሲያቀርቡ ነበር። መድረኩን ተቃወሙ ያሏቸውን ሁሉ በስማ በለው ያለ ማስረጃ አጣብቀው ሊያጠቁ ሲሞክሩ አንብበናል። በአሁኑ ጽሑፋቸው ደግሞ መድረኩ ምርጫውን አይርገጥ ያሉት ድርጅታዊ ብቃት ስለሌለው ህዝቡን አላደራጀም በሚል ነው። መድረኩ ይህን ባለማድረጉ አልወቅሰውም። ምርጫ አይግባ የምልበትም አንዱ መከራከሪያ ይሔው ነው። መድረኩም ሆነ አባል ድርጅቶቹ ለምርጫው በቂ ዝግጅት እንደያደርጉ በግልጽ ሲገፉ ቆይተዋል። እነ አቶ መለስ ያን ሁሉ ክልከላ አድርገው የቴያትሩ ወቅት ሲደርስ እየገደሉም ለጥቅማቸው ትንሽ ሞቅ ሞቅ ለማድረግ በተወሰኑ አካባቢዎች ስብሰባ ፈቅደዋል። አንድ ፓርቲ በዚህ መንገድ መብቱ ተገድቦ ቆይቶ ለቴያትሩ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ብቻ ና ተብሎ መጠራቱ ምርጫው በእንቅፋት ለመጀመሩ ማሳያ ነው። መድረኩ ህዝቡን ማደራጀት ስላልተፈቀደለት ከአምባገነኖች ጋር መላተሚያው ጊዜው አሁን አይደለምና በምርጫው መሳተፍ አለበት ይላሉ። ለዚህ ማጣቀሻቸው የቅንጅት መሪዎች የሀገርን ጥቅም ቢያስቀድሙ ኖሮ ትግሉን ወደፊት ማራመድ ይችሉ ነበር ብለዋል።

 

የቅንጅትን ጉዳይ በሀገር ውስጥ ሆኖ ጉዳዩን እንደተከታተለ አንድ ዜጋ ባየው ስህተቱ ምን ነበር? ብሎ በርጋታ መጠየቅን ይጠይቃል። ቅንጅት ፓርላማ ለመግባት ስምንት ነጥቦችን አንስቶ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠ። የህዝብ ድምፅ ተሰርቋል፣ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሠላምና ዲሞክራሲ መስፈን ሲባል በተጭበረተበረ መንገድ ሥልጣኑን ይዛችሁ ቀጥሉ ብሏል። ነገር ግን በ97 የተሠራው ስህተት የህዝብ ድምፅ መስረቁ፣ የንፁኀን ጭፍጨፋው፣ ሕገወጥ ድርጊቱ እንዳይደገም ለቀጣዩ ምርጫ 2002 ነፃ እንዲሆን ዋስትናችን ስምንቱ ነጥቦች ናቸው አሉ። ነፃ ፓርላማ፣ ነፃ የፍትህ አካላት፣ ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ የመከላከያ የፓሊስና የደህንነት ተቋማት ይመስረቱ አሉ። ከዚህ በላይ የሀገርን ጥቅም ማስቀደም ምንድነው? ዛሬ እነዚህ ተቋማት ቢኖሩ እኔና ፀሐፊው ምርጫ ይግቡ፣ አይግቡ የሚል ክርክር ባላነሳን ነበር። እነ ብርቱካኖችም በግፍ ባልታሰሩ። ከሰኔ አንድ የጭፍጨፋ በኋላ የጥቅምት 22ቱና ከዚያ በኋላ የተደረገው አይከሰትም ነበር። ዛሬም እነ አረጋዊ ገ/ዮሐንስ እና በያንሳ ዳባ በግፍ ባልተገደሉ።

 

የፀሐፊው ዓላማ መድረኩ በበሳል አመራር የእነዚህን ተቋማት ምስረታ ገፍቶ ከመጠየቅ ይልቅ በተጭበረበረው ምርጫ 2002 ይሳተፍ ምናልባትም ይቀጥል ነው። የቅንጅት መሪዎች የመምረጥ ፈተና ተጋርጦባቸው ነበር። ሕገ ወጥነትን መቀበልና አሜን ብሎ ተንበርክኮ እያለቀሰ ድምፄን አታዘርፍ ያላቸውን ህዝብ ምን ታውቃለህ ብለው መካድ ወይም መከራን መጋፈጥ። የውሳኔውን መጨረሻ በትክክል ያውቁት ነበር። በቅሎ ቤት በሚገኘው የዚያን ጊዜው የቅንጅት ቢሮ ተቃዋሚዎች ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ የሚሉትን ለመወሰን ሲሰበሰቡ ህዝቡ ከውጭ ሆኖ ይጠብቃል። እነ አቶ መለስ መሣሪያ የታጠቁ ፌደራሎች እና ልዩ ኃይል አፍሰው፣ የጦር ተሽከርካሪዎች ደርድረው “ዋ” እያሉ ነበር። ዛሬ ያንን መስዋዕትነት የከፈሉት መሪዎች ላይ ዘለፋ ከመሰንዘራችን በፊት የተሠራውን እና የሆነውን በጥልቅ መመርመርን ይጠይቃል። የነዚያን ንፁኀን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመጣ የከፈሉትን መስዋዕትን ከማጣጣልም መጠንቀቅ ይገባል።

 

የፀሐፊው መድረኩን ምርጫ ግባ ለማለት በአራተኛነት ያነሱት ነጥብ ሲጨመቅ ፍርሃት ነው። መድረኩ ምርጫ ካልገባ ያበቃለታል የሚል። የአቶ መለስ አስተዳደር መድረኩ የሥነ ምግባር ስምምነቱን አልፈረመም ካለበት ጀምሮ አንዴ በአሸባሪነት ሲለው በሻዕቢያ፣ በኦነግ እና በሕገ መንግሥት አፍራሽነት ሲከሰው ቆይቷል። ከዚህ አልፎ ማስረጃ ሰብስቤ ለመክሰስ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል። የተለመደውን የፈጠራ ወንጀል በመሪዎቹ ላይ ለማቅረብ ዝግጅት እንዳለ ያመለክታል። ፀሐፊው መድረኩ ህልውናውን ለመጠበቅ ምርጫ መግባት አለበት ይላሉ። እነ አቶ መለስ የሚያስፈራሩትም ለዚህ ነው። መድረኩ ጠንክሮ ህዝቡን አስተባብሮ የመደራደር አቅም እንዳይኖረው ለማድረግ ነው። ለመሆኑ መድረኩ እታገላለሁ ለሚልላቸው የሕግ የበላይነት፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቅድሚያ ይስጥ ወይስ ለድርጅቱ ህልውና ይቁም? ዛሬ ሕገ ወጥ ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ምርጫ ይግባ ያልነው መድረክ ነገ ለህልውናዬ ስል የህዝብን ድምፅ መሰረቁን እቀበላለሁ ቢል ልንቀበለው ነው? ይህ በጥልቅ ማሰብን ይጠይቃል።

 

“… መድረኩ በምርጫ ሂደት መሳተፉ በራሱ ያመጣቸው ውጤቶች አሉ በየክልሎች እየሄደ ህዝብን በማደራጀት ላይ ይገኛል። ህዝብ ለመብቱና ለነፃነቱ እንዲታገል፤ ከፍርሀት እንዲላቀቅ፣ በራሱ እንዲተማመን ቀንበርና ግፍ በቃኝ እንዲል ቅስቀሳ እየተደረገ ነው። ይህ መድረኩ ከምርጫው በፊት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ምርጫውም ካለቀ በኋላ እንዲቀጥሉ መደረግ አለበት። ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ ነው ህዝብ ተደራጅቶ አገዛዙን መጋፈጥ የሚችልበት ሁኔታ መፍጠር የሚችለው … በመሆኑም መድረኩ ሕጋዊነቱን እንደያዘ ቁልፍ የሆነው ህዝብን የማደራጀት ሥራ ይሠራ ዘንድ የግድ በመሆኑ መድረኩ ምርጫውን ይሳተፍ ዘንድ ይገባል አምስት በሉ …”

 

ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት ፀሐፊው በሦስተኛው የመከራከሪያ ነጥባቸው መድረኩ ህዝብ ስላላደረጀ ከሚጋፈጥ በበሰለ አመራር በምርጫው መሳተፉን ይቀጥል ብለዋል። ከላይ በጠቀስኩላቸው አንድ አንቀጽ ደግሞ አንዴ መድረኩ በየክልሎቹ ህዝቡን እያደራጀ ነው ዝቅ ብሎ ደግሞ ”… የማደራጀት ሥራ ይሠራ ዘንድ የግድ በመሆኑ …” መድረኩ ምርጫውን መሳተፍ አለበት ይላሉ። የመድረክ አመራሮች ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ካለ እናሸንፋለን ብለዋል። በሌላ በኩል ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አለመኖሩን የሚያሳይ በርካታ ማስረጃ ራሳቸው ገልፀዋል። መድረኩ ምርጫ አይግባ የሚሉ ወገኖች ህዝባዊ እንቢተኝነት የሚያመጣውን ኃይል ያምናሉ። ምርጫ ይግባ ባዮች ደግሞ አንዴ ህዝቡ ተደራጅቷል፣ ዝቅ ብሎ ደግሞ አልተደራጀም ይላሉ። መቼ አፋኝ ሥርዓቱ ፈቅዶ መድረኩ አደራጅቶ እንደሚጨርስ አይነግሩንም።

 

እኔ የመድረኩ አመራር ያለውን አምናለሁ። መድረኩ ለሕግ የበላይነት የሚያደርገውን ትግል ወደጎን አድርጎ፤ ለፓርቲው ህልውና ቅድሚያ ለመስጠት ብሎ በተጭበረበረው ምርጫ መሳተፍ ከዚያም እነ አቶ መለስ የሰጡትን ውጤት ተቀብሎ መቀበል አለበት አልልም።

 

“መድረኩ ከምርጫው እራሱን ቢያገል ኢህአዲግ “አጭበረበረ” ማለት አይቻልም በፎርፌ አሸንፏል። አጭበረበረ ማለት የሚቻለው በምርጫው ተሳትፎ በርግጥ መሰረቁን በማጋለጥ ነው …” የሚል ስድስተኛ የመከራከሪያ ነጥብ ቀርቧል። ፀሐፊው ቀደም ብለው “የምርጫውን ውጤት የሚወስነው ድምፅ ሰጭው ሳይሆን ድምፅ ቆጣሪው ነው። ቆጣሪው ኢህአዲግ በሆነበት ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ በምንም መስፈርት ነፃና ዲሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም” ብለዋል። በአንድ በኩል የምርጫውን መጭበርበር ለማወቅ ቅድመ ምርጫው የሚያሳየው በቂ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ሃሳብ ተቃዋሚዎች አስቀድሞ የተጭበረበረውን የምርጫ ሂደት ረግጠው ይውጡ ከሚሉት ጋር ይስማማሉ። መልሰው ደግሞ የለም የድምፅ መስጫውን ዕለት መጠበቅ ነው ይላሉ።

 

አንድ የምርጫ ተወዳዳሪ ከምርጫ ረግጦ የሚወጣው ፋሽን ስለሆነ አይደለም። ያ ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ የማይሆንባቸው ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ነው። ምርጫ 2002 በቅድመ ምርጫ ሂደቱ ተጭበርብሯል። የምርጫው ዕለት የሚለውጠው ነገር የለም። ይልቅ እነ አቶ መለስ አስቀድመው ያረጋገጡትን ውጤት ለማጠናቀቅ የቀራቸውን ድራማ በሚገባ ለመተወን የምርጫውን ዕለት ብቻ ነው የሚጠብቁት። በዚህ ዕለት አጭበርብረው ለራሳቸው ሕጋዊ ሽፋን እንዳይሰጡ ለማድረግ የሚቻለው እውነተኛ ተቃዋሚዎች ይህን ምርጫ ረግጠው በመውጣት ዕቅዳቸውን ሲያከሽፉባቸው ብቻ ነው።

 

በመጀመሪያው ጽሑፌ ሁሉም እንደሚያውቀው ብርቱካን የታሰረችው ለሕግ የበላይነት ነው። ቃሌ የሚለውን ጽሑፏን ደጋግሞ ማየት ይገባል። መድረኩ ምርጫውን ረግጦ ቢወጣ ብርቱካን የታስረችለት፣ እነ በያንሳ ዳባ፣ አረጋዊ ገብረዮሐንስ የሞቱለትን የሕግ የበላይነት መደገፍ ነው ብዬ ነበር።

 

ፀሐፊው መድረኩ ምርጫው ውስጥ ካልገባ የብርቱካን ጉዳይ ይረሳል፣ ባገር ቤት ጉዳይዋን አንስቶ የሚከራከር ይጠፋል ብለዋል። ሰባተኛው መከራከሪያ ነጥባቸው ይሄ ነው። ደጋግመው የፃፉትን ካልዘነጉት ብርቱካን መስዋዕትነት እየከፈለች ያለችው በሕገ ወጥ እስር ነው። ሕገ ወጡን ውሳኔ አልቀበልም ብላ ነው። ምርጫዋ ለሕግ የበላይነት መቆም ወይም ለእነ አቶ መለስ ሕገ ወጥ ቅድመ ሁኔታ ተንበርክካ የግል ምቾቷን ጠብቃ መቀጠል ነበር። በቃሏ እንዳለችው የምትታሰርለት ምንአልባትም የምትሞትለት የሕግ የበላይነት እና ሕጋዊነት በመሆኑ መከራ እየተቀበለች ነው። በመከራዋ ዋዜማ ግን አናውቅልሽም ብለው የከዷት ጥቂት የፓርቲ አመራሮች ነበሩ። እነ ፕሮፌሠር መስፍን ይህችን ካርድ መዘው በመጨረሻ ሰዓት ለነመለስ መጠቀሚያ ከማድረግና ፓርቲ እስከ ማፍረስ ከመሄድ በውስጥ ትግል ማድረግ ሲገባቸው ረግጠው ወጥተዋል። ለኔ ለሕግ የበላይነት ተሟጋችነት አሁን ባሉትም ጥቂት ብርቱካንን በካዱት አመራሮችም ሆነ ተገንጥለው በወጡት “ዝም አንልሞች” እሷ መከራ እየተቀበለች ያለችለት የሕግ የበላይነት አልተከበረም።

 

መድረኩ ብርቱካን የታሰረችለትን የሕግ የበላይነትን ወደ ጎን አድርጎ እነ አቶ መለስ እንዳይጨፈልቁት ነፍሱን ያቆይ ማለት በየትኛው መስፈርት ተቀባይነት ይኖረዋል? አቶ አረጋዊ ገብረዮሐንስም ሆነ በያንሳ ዳባ ሕገ ወጥ አማራጭ ቀርቦላቸው ነበር። ከፓርቲ ሥራ እራሳቸውን ማግለል ወይም መጋፈጥ። በሕይወታቸው ዋጋ ሲከፍሉ ፓርቲያቸው ግን ለሕገወጥ ቅድመ ሁኔታ ተንበርክኮ የሕጋዊነት ተሟጋች መሆን መቼ የተጀመረ ሂሳብ ነው? ምላሹን መድረኩ ምርጫውን ረግጦ አይውጣ ለሚሉት እተዋለሁ።

 

“ብዙዎቻችን ምርጫውን እንደቀልድና ጨዋታ ብንወስደውም ህዝብ ውስጥ የታመቀው የነፃነት እሳት ተዓምር ሊፈጥር እንደሚችል መዘንጋት የለብንም። … ቢሆንም የህዝብ ተዓምር የመሥራት ዕድልንም ስለሚከፍት መድረኩ በምርጫው ይሳተፍ ዘንድ ይገባል። ስምንት በሉ” ብለውናል።

 

ህዝብ ተዓምር አይሠራም ብየ አላምንም። ተቀባይነት ያለው ሃሳብ ነው። ችግሩ መድረኩ ይህንን ተዓምር የሚሠራ ህዝብ ማስተባበር ትቶ አስቀድሞ በተጭበረበረ ምርጫ ይሳተፍ ከሚሉት ላይ ነው። በአንድ በኩል መድረኩ ህዝብ አደራጅቷል እንላለን። የህዝብ ድጋፍ እንዳለው አያጠራጥርም። ከህዝቡ ኃይል ይልቅ የእነ አቶ መለስን ጡንቻ አግዝፈን እንደ ፀሐፊው ወዮላችሁ ምርጫ ካልገባችሁ የትግል ፍፃሜ ሆነ ማለት ግን የሚጋጭ ነው።

 

የመድረኩን እንቅስቃሴ አልቃወምም። አስቀድሞ በተጭበረበረው ምርጫ ግን መሳተፍ አለበት ብዬ አላምንም። የተጭበረበረው ምርጫ የሚጠቅመው እነ አቶ መለስን የሕጋዊነት ካባ ለማልበስ ብቻ ነው። ለዚህ እምነቴ መነሻ የሆኑኝን ነጥቦች ላስቀምጥ።

 

የመድረኩን መሪዎች ጨምሮ አብዛኛው ወገን እንደሚስማማበት የምርጫ አስፈፃሚዎች ገለልተኛ አይደሉም። የምርጫ ቦርድ አወቃቀር እንዲስተካከል ተደጋግሞ ተጠይቋል። የሰማው የለም። በአቶ መለስ የበላይነት የሚመራው የምርጫ ቦርድ ነው። በዚህ ገለልተኛ ባልሆነ ቦርድ አማካይነት የሚካሄድ ምርጫ ህዝብ የሰጠውን ድምፅ የማያስከብር ነው። በምርጫው የዕጩዎች እና የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በጉልህ ገለልተኛ አለመሆኑን አስመስክሯል። የዜጎችን የመምረጥ በመብት በመጋፋት በአንዳንድ አካባቢዎች በተቃዋሚነት የሚጠረጥራቸውን ከምርጫ ውጭ እንዲሆኑ ሲገፋ ነበር። የሚፈልጋቸውን ደግሞ ከምርጫ ሕጉ ውጭ መዝገብ ይዞ እየዞረ መዝግቧል። ይህ ገለልተኛ ያልሆነ አካል 29 ሚሊዮን መራጭ ተመዝግቧል ቢልም ቁጥሩን ልኮለታል ከሚባለው የኢህአዲግ ጽ/ቤት ሌላ ያመነው አልተገኘም። ታዲያ ይህ ቦርድ እንዴት ብሎ ነው በገለልተኝነት ምርጫውን አካሂዶ የሚሰጠው ውጤት ተቀባይነት የሚኖረው? የመድረኩ በዚህ ምርጫ አለመሳተፍ የቦርዱን ገለልተኛ አለመሆን የሚያረጋግጥና ቀጣዩን ትግል ህዝቡን አስተባብሮ ኢህአዲግን በግድ ለድርድር በማምጣት ገለልተኛ ቦርድ እንዲቋቋም መጠየቅ ይኖርበታል። አንድ በሉ።

 

የአንድን ምርጫ ፍትሃዊነት ከሚያረጋግጡ አብይ ጉዳዮች አንዱ የገለልተኛ ታዛቢዎች ጉዳይ ነው። ተደጋግሞ እንደተገለፀው እነ አቶ መለስ ለምርጫ 97 ዋነኛ ሽንፈት ያበቃን ያገር ውስጥ እና የውጭ ታዛቢዎች ናቸው ብለው ያምናሉ። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በሀገር ውስጥ በታዛቢነት ከተሰማሩ ድርጅቶች መካከል መታሰር አለባቸው ያሏቸውን አሰሩ። ነፃነት ደምሴን እና ዳንኤል በቀለን ይጠቅሷል። በዚህ አልበቃቸው ብሎ ተቋማቱን ለማጥፋት የአሜሪካን መንግሥትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት የተወገዘውን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ አዋጅ አውጥተዋል። በዚህ አዋጅ መሰረት በ97 ምርጫ እንደታየው ለምርጫው 48 ሰዓት ሲቀረው ምርጫ ለመታዘብ የተፈቀደላቸው የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ዘንድሮ የሉም።

 

በዚህ ያልበቃቸው አቶ መለስ በአምሳያቸው የቀረጿቸውን ጥቂት ድርጅቶች በሀገር ውስጥ ታዛቢ ስም ዘንድሮ ያሰማራሉ። ከምርጫው በኋላ ለነዚህ ድርጅት ተወካዮች ሰፊ መድረክ በመስጠት የዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን ለማሳጣት ቀድመው ምርጫው ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን በመናገር ምስክርነት ሰጡ ለማለት ዝግጅቱን አጠናቀዋል። የውጭ ታዛቢዎችን ሆን ብለው ቶሎ አልጋበዙም። በተጣበበ ሂደት እንዲመጡ ከማድረግ አልፈው የመግባቢያ ሰነድ አዘጋጅተው አስፈርመዋል። የካርተር ማዕረል ይህን ባለመቀበሉ ተጋብዞም አልመጣም ብሏል። የአውሮፓ ሕብረት ዘግይቶ ወስኖ በቅርቡ የምርጫ ሂደቱን ለመታዘብ ወደ ክልል ተሰማርቷል። ይህ የአውሮፓ ምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ብዙ ቴአትር ይጠብቀዋል። ከሩቁ የሚከታተሏቸው መረጃ እያቀባበሉ እነሱ (ቁጥራቸው ከሁለት መቶ አይበልጥም) በሚደርሱባቸው ቦታዎች የተወሰኑ ማስመሰያዎች ለመሥራት ዝግጅት ተደርጓል። የህዝብ ታዛቢ ተብዬዎቹ በኢህአዲግ የተመረጡ ከ200 ሺህ በላይ አባላቱና የሥርዓቱ ደጋፊዎች በመሆናቸው ለቴአትሩ ሰልጥነዋል። በስፍራው የሚገኙት የተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲዎች በተለይም የመድረኩ ታዛቢዎች በከፍተኛ ጫና ስር ይወድቃሉ። የተጭበረበረው የምርጫ ውጤት በነዚህ ሰዎች እየተፈረመ ሕጋዊ እየተባለ ይለጠፋል። ቦርዱ በ97 ምርጫ የሠራው ስህተት እነ አቶ መለስን ለመጥቀም አንዳንድ ቦታዎች ከተመዘገበው መራጭ ቁጥር በላይ ኢህአዲግ ያገኘው ቁጥር በልጦ የተለጠፈበትን ስህተት ላለመድገም ይሞክራሉ። ያኔ ውጥረቱ ከታዛቢዎች ነበር። ዛሬ ያለከልካይ የህዝቡን ድምፅ ይጫወቱበታል። መድረኩ በዚህ ሂደት ባይሳተፍ እና ረግጦ ቢወጣ የምርጫ ታዛቢዎች ገለልተኛ አይደሉም ያለውን ጥያቄውን ያጠነክረዋል። ለገለልተኛ ታዛቢዎች መኖር ትግሉን ይቀጥላል ሁለት በሉ።

 

በኢትዮጵያ የነፃ ሚዲያ መታፈን አያከራክርም። ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገቡ ሥርዓቱ የማይፈልጋቸው የሬዲዮ ስርጭቶችንም ጭምር ህዝቡ እንዳያዳምጥ ተከልክሏል። የኢትዮጵያ ህዝብ እየተራበ አገዛዙ መረጃ ለማፈን ገንዘብ ያባክናል። የህዝቡ ድምፅ ሊሰማበት የሚገባውን መገናኛ ብዙኀን ላለፉት 19 ዓመታት ያንድ ዘረኛና አምባገነናዊ ቡድን ጥቅም ማስከበሪያ አድርጎታል። በምርጫ 97 የነፃ ፕሬስ ውጤቶች የተጭበረበውን የምርጫ ውጤት እና ተከትሎ የመጣውን ጭፍጨፋ በማጋለጥ የተጫወቱትን ሚና ለማዳፈን በርካታ ጋዜጦችን አግዷል። ጋዜጠኞችን አስሯል። ብዙዎች ስደት ዕጣቸው ሆኗል። በሀገር ውስጥ እሱ ከሚፈልጋቸው ውጭም ፈቃድ አይሰጥም። ጋዜጠኞችን በአሸባሪነት ለመክሰስ ሕግ አውጥቷል። የዚህ ክስ መረጃ የደረሳቸው የአዲስ ነገር ጋዜጠኞች ሀገር ለቀው ተሰደዋል። አንዳንዶች ዛሬም ጉሸማ እየበዛባቸው ነው። በመጭው ምርጫ የገለልተኛ ሚዲያ አለመኖር እና የምርጫውም ሂደት ሆን ተብሎ እንዳይዘገብ የተጣለው አዲሱ የምርጫ ቦርድ የደንብ ገደብም ይጠቀሳል። ምርጫው ፍትሐዊ ከማይሆንባቸው መስፈርቶች የሚዲያ ነፃነት አለመኖር መሆኑን መድረኩ ገልጾ ረግጦ ቢወጣ ትግሉ ሚዲያው ነፃ ይሁን የሚል ጥያቄ ይሆናል። ሦስት በሉ።

 

የምርጫው ሂደት አስቀድሞ ተጭበረበረ። የምርጫው ዕለት ይሔው ይደገማል። መድረኩ ይህንኑ ገልጾ የተሰረቀውን የህዝብ ድምፅ ለማስከበር የሚያስችልበት አማራጭ የለውም። የፍትሕ አካሉ ገለልተኛ አይደለም። በቀጥታ በፍትሕ ስም የእነ አቶ መለስን ውሳኔ እየተቀበለ የሚያነብ ነው። ለዚሕ ሩቅ ሳንሔድ ከመድረኩ መሪዎች አንዱ የሕግ የበላይነትን አስመልክቶ ከጻፉት መረዳት ይቻላል። በእነ አቶ መለስ ዕቅድ መሰረት በምርጫው ቅሬታ ያለው በሙሉ በቀጥታ ነፃነቱን ከገደሉት ፍርድ ቤት መሔድ አለበት። የዚህን ገለልተኛ ያልሆነ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተቀብሎ ምርጫ ቦርድ የዘረፈውን የህዝብ ድምፅ ግብዓተ መሬት በፍትሕ ስም በቆሙ ፍርድ ቤቶች አስቀብሮ አርፎ የመቀመጥ ግዴታ ተጥሎበታል። እነ አቶ መለስ የፍርድ ቤት ውሳኔ የሚያከብሩት ለራሳቸው ብቻ እስከተመቻቸው ድረስ መሆኑን የብርቱካንን ጉዳይ በቀላሉ ማንሳት ይበቃል። ፍ/ቤት በሕገመንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠውን የእስረኛ በሐኪም፣ በጠበቃ፣ በቤተሰብና በጓደኛ የመጎብኘት መብት ነው ሲል እነሱ አትጠየቅም ብለዋል። በምርጫ ጉዳይ ጨርሶም ፍርድ ቤቱ ተጭበርብሯል እንዲል አይፈቅዱለትም። መድረኩ ምርጫ ረግጦ ቢወጣ ይህን የይስሙላ ሂደት በማስቀረት ለአንድ ምርጫ የፍትሕ አካላት ነፃነት የግድ አስፈላጊ መሆኑን በቀጣይ ትግሉ ማሳየቱን ይቀጥላል። አራት በሉ።

 

የአንድ ምርጫ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊነት ከሚረጋገጥባቸው ጉዳዮች አንዱ የመራጩ ህዝብ ድምፁን በነፃ ለመስጠት ያለው ነፃነት ነው። የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች (የፖሊስ፣ የደህንነት፣ የመከላከያ፣ የሚሊሻ እና ልዩ ልዩ ስም የተሰጣቸው ታጣቂዎች) ከአንድ ፓርቲ ወገንተኝነት ነፃ መሆን አለባቸው። በምርጫ 97 የታየውን የእነዚህን ተቋማት ግፍ ፈጻሚነት ለቀባሪው ማርዳት ነው። የአቶ መለስ አስተዳደር ከምርጫው ቀን ቀድሞ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ አስቀድሞ ህዝቡን ለማስጨፍጨፍ ተዘጋጅቶ በፈለገው ቀን ድምፄ ይከበር ያለው ህዝብ ላይ ተኩሶ ከሁለት መቶ የበለጡ ንጹኀንን ገድሏል። በዚህ ግድያ ከ14 ዓመቱ ሕጻን ነብዩ እስከ ባሌን አትውሰዱት እስካሉት ባልቴት ሕይወታቸው አልፏል። ማን ያልተገደለ አለ? የፓርላማ ተመራጭ፣ የፓርቲ አባል፣ ሕጻን፣ ሽማግሌ፣ ሴት፣ ወጣት፣ … ሁሉም በግፍ ተገለዋል።

 

ዘንድሮም የፀጥታ ኃይሉ (ሚሊሻውን ጨምሮ) ከጩቤ እስከ ቦንብ ውርወራ ሔዶ ማጅራት መምታቱን ቀጥሏል። ግድያው፣ ድብደባውና አፈናው የምርጫው ዕለት እና ከዚያም በኋላ አይቀርም። በቅድመ ምርጫው በግፍ የተገደሉትን ሰማዕታት ደም ለመፋረድ መድረኩ ይሔን ጥያቄ በማንሳት ምርጫውን ረግጦ መውጣት አለበት። ቀጣይ ትግሉም ይህ ኃይል ፍትሃዊ እና ነፃ በሆነ መንገድ ይደራጅ ብሎ ታግሎ ማታገሉን ይቀጥላል። አምስት በሉ።

 

የመድረክ ትግል የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ሀገር እንድትኖር ከሆነ ሕልሙ በተጭበረበረ ምርጫ ተሳትፎ የአምባገነኖች ዕድሜ ማራዘሚያ መሆን አይደለም። ስለዚህ ግቡ ቀድሞ ካለቀው የዘንድሮ ምርጫ በሚመሰረተው ነፃነት በሌለበት ፓርላማ መግባት እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ምርጫውን ረግጦ ሲወጣ በቀጣይ ትግሉ ነፃ ፓርላማ ተቋቁሞ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር መሥራት ይሆናል። ይህን ካላደረገ በምርጫ 97 ፓርላማ የገቡት የተወሰኑት የመድረኩ መሪዎች በተለያየ ስፍራ በሰጡት መግለጫ ፓርላማ ገብተን ያመጣነው የለም ብለዋል። መድረኩ አስቀድሞ በተጭበረበረው ምርጫ ቢሳተፍ እነ አቶ መለስ ጫማቸው ስር አድርገው የፈለጋቸውን ሕገ ወጥ አዋጅና ውሳኔ በሕጋዊነት ስም የሚወስኑበት ፓርላማ ከዝርፊያ የተረፉ ጥቂት ወንበሮች ይዞ ማጀብ ነው። መድረኩ ምርጫውን ረግጦ ሲወጣ ለነፃ ፓርላማ መኖር ትግሉን ይቀጥላል። ስድስት በሉ።

 

መድረኩ ከላይ የተዘረዘሩትን ሕጋዊና ተቀባይነት ያላቸውን እርምጃዎች በማጤን አስቀድሞ የተጭበረበረውን ምርጫ ረግጦ ቢወጣ የነ አቶ መለስን ቴአትር ያደናቅፋል። በዚህ እርምጃው የቆመለትን የሕግ የበላይነት ይደግፋል። ብርቱካን ለቆመችለት እና የግፍ እስር እየተቀበለችለት ላለው ዓላማ የሚታገል መሆኑን ጭምር ያረጋግጣል። የእነ በያንሳን ገዳዮች ለመፋረድ ይቆማል። ስለዚህም መድረክ አስቀድሞ የተጠናቀቀውን የቀልድ ምርጫ ረግጦ በመውጣት ቁምነገር ሊሠራ ይገባል እላለሁ።


ሀብታሙ አሰፋ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ