ድርጅታዊ አቅም ሳይገነቡ ስሜታዊ እርምጃዎች መውሰድ ጉዳት አለው
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
በቅርቡ «ምርጫው ቀልድ ነው፤ መድረኩ ግን ቢሳተፍ ይበጀዋል» በሚል ርእስ ለአንባቢያን ባቀረብኩት ጽሁፍ ላይ ባነሳኋቸው አንዳንድ ነጥቦች ላይ፣ የማውቃቸውና የማክበራቸው ወዳጄ፣ አቶ ይልማ በቀለ የሰጡትን ምላሽ አነበብኩ። አቶ ይልማ በተለያዩ የአገራችን ጉዳዮች ላይ ትምህርት ሰጪ መጣጥፍት የሚያቀርቡ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ የዲሞክራሲ ታጋይ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ለሚያደርጉት አስተዋጾና ጥረት ላመሰግናቸው እወዳለሁ።
አቶ ይልማ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ላይ ጠንካራ የተቃውሞ አቋም መውሰዳቸው ይገባኛል። ነጻነት በልመና የሚገኝ አይደለም። ነጻነት መስዋእትነትን ይጠያቃል። ነጻነት ነጻ አይደለም። በመሆኑም ለነጻነት በሚደረገው ትግል ሥር ነቀል እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ ግፊት ማድረጋቸው ተገቢ ነው። እኔም ሆነ አብዛኞቻችን የምንደግፈውና የምንጋራው ነው።
አንድ አቶ ይልማ ከጻፉት ደስ ያለኝን አባባል ልጥቀስ። «ለነጻነት ቀጠሮ አይገባውም ፤ ነውር ነው።» ነው ያሉት። በጣም ትክክለኛ አባባል ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የመጀመሪያ ጊዜ ቃሊቲ እሥር ቤት በነበረችበት ጊዜ «ሰው ያለ ነጻነቱ ምንድን ነው» ነበር ያላቸው። የሰው ልጅ እግዚአብሄር ሲፈጥረው ነጻ ሆኖ እንዲኖር ነው። ነጻነት የሌለው ህዝብ እንደ ህዝብ ሊቆጠር አይችለም።በመሆኑም ለነጻነት የሚደረግ ትግል በዝግታ፣ በቀጠሮ፣ በቸልተኝነት ሊደረግም አይገባም። የአቶ ይልማን አባባል ልዋስና «ነውር» ነው።
ይሄን ብዬ አቶ ይልማ ወዳነሷቸውና ወደማልስማማባቸው አንዳንድ ነጥቦች ልመለስ።
አቶ ይልማ - «በመላው ጽሑፉ ሊቀመንበር ብርቱካን የምትጠራው ወ/ት ብርቱካን ተብላ መሆኑ ምክንያቱ አልገባኝም» ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
«ሊቀመንብር ብርቱካን» ከማለት «ወ/ት ብርቱካን» ማለቴ አቶ ይልማን ያስከፋቸው ይመስላል። ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚገባውን ክብር እንዳልሰጠው፣ መሪነቷንም እንደማልቀበል አስበው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። እንደዚያም ከሆነ ደግሞ ምንም ማድረግ አልችልም። የመሰላቸውን የማሰብ ሙሉ ነጻነት አላቸው። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለዚች ለማከብራት እህቴ ያለኝ ፍቅር ለአቶ ይልማም ሆነ ለማንም የማስረዳት ግዴታ ያለብኝ አይመስለኝም። በመሆኑም ይሄን ጉዳይ በዚህ እዘጋዋለሁ።
«መድረኩም ቢሆን አንድነት የሊቀመንበሯ አንደኛ ተሟጋች ናቸው ማለት እውነትን እንደማጣመም ይቆጠራል። በቅርብ ጊዜ እንኳ ሕመሟን ለዓለም ያስታወቁት ወዳጆቿ ናቸው እንጂ ጓዶችዋ ነን ባይዎች አይደሉም። በዳያስፖራውም የሊቀመንበሯን ጉዳይ በትጋትና ባለመሰልቸት የሚያካሂዱት በፈቃደኝነት የተቋቋሙት ድርጅቶች ናቸው እንጂ በሰሜን አሜሪካ ያለው የአንድነት ደጋፊ ቡድን አይደለም።» የሚልም አቶ ይልማ በጻፉት ጽሁፍ ላይ አንብቢያልሁ።
ይህ ቀጥተኛ የሆነ አገር ቤት ባለው የአንድነት/መድረክ አባላት ላይ እና በውጭ አገር ባሉ የአንድነት የድጋፍ ማህበራት ላይ የተሰነዘረ ክስ ነው።
አቶ ይልማ በሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ማህበር አባል የሆነው የኦክልናድ ድጋፍ ማህበር አመራር አባል እንደሆኑ ነው የማውቀው። የኦክላንድ ቻፕተር ሊቀመንበር ሆነው ያገለግሉበት ወቅትም ነበር። ሌላ ሰው በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር ላይ ይህን አይነቱን ትችት ቢያቀርብ ባልከፋ ነበር። ነገር ግን የሚደረገውንና የሚሰራውን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ የድጋፍ ማህበሩ በየጊዜው አዲስ አበባ ካሉ የአመራር አባላት ጋር የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች የሚካፈሉ፣ ብዙ በአገር ቤት ስለሚደረገው እንቅስቃሴ እውቀት ያላቸው ወገኖች ግን ይህን አይነት አስተያየት ሲሰጡ ትንሽ ግር ይላል።
እንደዚያም ሆኖ ደግሞ ይሁን ከተባለ፣ ይህን አይነት ክስ በትግል አጋሮቻቸው ላይ ሲዘነዝሩ መረጃና የተጨበጠ ነገር ቢያቀርቡልን ኖሮ የበለጠ ጥሩ ይሆን ነበር።
የሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ድርጅቶች ማህበር በአሜሪካን አገር ያሉ በርካታ የድጋፍ ማህበራትን ያሰባሰበ አካል ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በርካታ የአንድነት ድጋፍ ማህበራት (የዲስ የሎስ አንጀለስ፣ አትላናት ….) ወ/ት ብሩትካን ሚደቅሳ እንድትፈታ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በየጊዜው በአለም ዙሪያ የሚደረጉ የሰላማዊ ሰልፎችን የአንድነት ድጋፍ ማህበራት ናቸው ከተለያዩ የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት። በዋሺንገተን ዲስ በየወሩ በደማቅ ሁኔታ የቃሌ ምሽት ይደረጋል። ይህንን የሚያደራጁት የዲሲ ሜትሮ የአንድነት ድጋፍ ማህበር ናቸው። ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ቤተሰብ ጋር በዋናነት የሚገናኝና የብርቱካን ጉዳይ የሚከታተለው የሰሜን አሜሪካ አንድነት ድጋፍ ማህበር ድርጅት ነው። ይህን ሁሉ አቶ ይልማ ያጡታል ብዬ አላስብም።
እዚህ ላይ ገንቢ ወቀሳ በሰሜን አሜሪካ የአንድነት ድጋፍ ማህበር ላይም ሆነ ማንም ድርጅት ላይ ማቅረቡን ጠልቼው አይደለም። «ጥረታችሁ ሁለት ሶስት እጠፍ መሆን አለበት፤ በቂ አይደለም» ማለትና በጨዋነት መውቀስ የአባት ነው። መሰረት የሌለው ተራ አሳዛኝ ክስ ማቅረብ ግን ነውር ነው።
አገር ቤት ያለውን የአንድነት ፓርቲና መድረኩ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ በቅርቡ ለአንባቢያን ባቀረብኩት ጽሁፍ የሚከተለውን ብዬ ነበር ፡
«በኢትዮጵያ ውስጥ የብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ብቸኛ ድርጅት የአንድነት ፓርቲ ነው። የአንድነት ፓርቲ በሚያደርጋችው ህዝባዊ ስብሰባዎች ሁሉ የብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ሕገ-ወጥ እንደሆነ በመቀስቀስ፣ ህዝቡ እንድትፈታ እንዲታገል ግፊት እያደረገ ነው። በመስቀል አደባባይ የተጠራው ሠላማዊ ሰልፍ ቢከለከልም፣ ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ የአንድነት አባላት የእርሷን ጉዳይ ከማንሳትና ለእርሷም ከመሟገት የቦዘኑበት ጊዜ የለም። በቴሌቭዥን በሚደረጉ ክርክሮች የብርቱካን ጉዳይ ይነሳል። የአንድነት ፓርቲ ወጣቶች የብርቱካን ኬኔተራን እየለበሱ ከኔቴራውን በመሸጥ ታስረዋል። ለብርቱካን የሻማ ማብራት ዝግጅት ላይ ለመካፈል ሁለት ቀናት ሙሉ በእግር ተጉዘው የሚመጡ ኢትዮጵያውያን አሉ። ትላንት ”ስለብርቱካን ምንም አይባልም” እያሉ ሲከሱ የነበሩ፤ ዛሬ ደግሞ ”የርሷን ስም አሥር ጊዜ እያነሱ መጠቀሚያ እያደረጓት ነው” እስኪሉ ድረስ የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም መድረኩ የብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ ዋና አጀንዳው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው»
በዚህ ላይ አቶ ይልማ አይስማሙ። «መድረኩም ቢሆን አንድነት የሊቀመንበሯ አንደኛ ተሟጋች ናቸው ማለት እውነትን እንደማጣመም ይቆጠራል» ሲሉ የአንድነት ፓርቲ የብርቱካን ሚደቅሳ አንደኛ ተሟጋች እንዳልሆነ ገልጸዋል።
እሺ ችግር የለኝም እዚህ ላይ። አንድነቱ በአገር ቤት አንደኛ የብርቱካን ሚደቅሳ ተሟጋች አይደለም እንበል። ማን ነው ታዲያ አንደኛ የብርቱካን ሚደቅሳ ተሟጋች ? አቶ ይልማ የሚያውቁት ቡድን ወይንም አካል ካለ ይንገሩን። እርሳቸው ሌላ አንደኛ የሚሉት አካል እስካላቀረቡ ድረስ ግን፣ አንድነቱ/መድረኩ አንደኛ የብርቱካን ሚደቅሳ ተሟጋች አይደለም የሚል መከራከሪያቸው ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም።
እርግጥ ነው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰረችበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት የአንድነት ፓርቲ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በማስፈታት ዙሪያ፣ ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አደረገ ማለት አይቻልም። ለዚህም ምክንያቱ በድርጅቱ ውስጥ በመድረኩ ዙሪያ የተፈጠሩት አለመግባባቶች ድርጅቱን አስረው በመያዛቸው ነበር። በሃሳብ ልዩነቶች ከድርጅቱ የሚለዩት ተለይተው፣ ድርጅቱ እራሱን አዋቅሮ ፣ አዳዲስ አመራር አባላትን አቅፎ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግን አመርቂ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው።
በአገር ቤት የሚታግል ደርጅት ኃይሉ የሕዝብ ድጋፍ ነው። ትልቁ ሥራው ህዝብን ማደራጀትና ማስተባበር ነው። የተከፋፈለውን ሕዝብ በአንድ ላይ ማምጣት ነው። የአንድነት ፓርቲ አባላት የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ጉዳይ ህዝብ ጋር ይዞ በመሄድ እንዳትረሳ፣ ህዝብ እርሷን እንዲያስብ፣ ለርሷ እንዲታገል ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። ከዚህ ውጭ መቼም ጠመንጃ ይዘው እንዲነሱ ከሆነ አቶ ይልማ ፍላጎታቸው ይሄ እንደማይሆን በዚሁ አጋጣሚ ልገልጽላቸው እወዳለሁ። እቅጩን ይወቁት።
«በቅርብ ጊዜ እንኳ ሕመሟን ለዓለም ያስታወቁት ወዳጆቿ ናቸው እንጂ ጓዶችዋ ነን ባይዎች አይደሉም» ያሉት አባባል ደግሞ አስገርሞኛል። «ወዳጆቿ» የተባሉት እነማን እንደሆኑ ብናወቅ ጥሩ ነበር።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የአንድነት ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለነጻነት ጥማት ላላቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ መሪ ናት። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችው እኛ በርሷ ስም ሌላውን እንድናቃልል፣ የተጨበጠ ነገር ሳንይዝ በአሉባልታ እንድንተች፣ እንድንከፋፈል አይደለም። የታሰረቸው የርሷን አላማ ይዘን ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነው ትግል ወደፊት እንድንገፋ ነው። የታሰረቸው ተስፋ ቆርጠን አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ሜዳውን ለኢሕአዴግ በመልቀቅ የስደት ትግል እንድናደርግ አይደለም። የታሰረችው ለአላማ ነው።
አላማዋ ደግሞ ምርጫ መሳተፍ ወይንም አለመሳተፍ አይደለም። ምርጫ የሂደቶች ሁሉ አንዱ ፋክተር ነው። አላማዋ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነቱን እንዲያገኝ ነው። ይህ ደግሞ ሥራ ይጠይቃል። ዝግጅት ይጠይቃል። ህዝብን ማደራጀት ይጠይቃል።
ጦርነት ለመግጠም ወታደሮች መሰልጠን አላባቸው። አቶ ይልማ ሳይሰለጥን ወታደር ጦር ግንባር አሁን ካልሄደ ነው የሚሉን። እኛ ደግሞ ዝግጅት ያስፈልጋል፤ ሥራ ያስፈልጋል፤ ህዝብን ከላይ እስከ ታች ማደራጀት ያስፈልጋል፣ አቅም መገንባት ያስፈልጋል» እንላለን። ከምርጫው መውጣት አይበጅም ስንል መድረኩ ያለውን ብቃት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕልውናው ላይ አደጋ እንዳይፈጥር በማሰብ ነው። ድርጅታዊ ጥንካሬያችን አስተማማኝ ሳይሆን ጉልበተኞችን መግጠም ከትርፉ ጉዳቱ ይበልጣም ብለን ነው።
እንግዲህ የክርክሮቹ መሥመሮች ሁለት ናቸው። በአንድ በኩል አገር ቤት የሚታገሉትን የሚከሱ፣ አገር ቤት ያለውን ትግል የሚያሳንሱ ወገኖች አሉ። ሌላውን ከመክሰስና በሌላው ሥራ ገብቶ ከመበጥበጥ ውጭ ፣ እነርሱ ያመነጩት፤ እነርሱ አንድ እርምጃ ያስኬዱት፣ የሚታይና የሚጨበጥ አማራጭ የላቸውም። ባዶ እጃቸውን ናቸው። እነርሱን ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ሌላውን ግን «ወያኔ» ፣ እነርሱን ለብርቱካን ተቆርቋሪ ሌላውን ግን ብርቱካንን የካደ ፣ እነርሱን ጀግኖች(ዳያስፖራ ሃምበርገራቸውን እየገምጡ) በእሳት ውስጥ በአገር ቤት እየታገለ ያለውን እንደፈሪ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው።
ለምሳሌ አቶ ይልማ ያቀረቡልን አንዳች አማራጭ የለም። ምርጫውን ቦይኮት ማድረግ ምን ጥቅም እንዳለው አልገለጹልንም። የራሳቸውን ጠቃሚ ሴንስ የሚሰጥና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መፍትሄ አላስቀመጡልንም። «ይሄ ቡድን ይሄን አልሰራም፤ ያኛው ደግሞ ይሄን አላደረገም» ብሎ ከመተቸት ውጭ «ይህንን በዚህ መንገድ ብናደርግ፣ ይህን ችግር በዚህ በኩል ብንፈታው፤ በዚህ መንገድ ከምንሄድ በዚህ ና በዚያ ምክንያቶች፣ ያኛውን መንገድ ብንከተል ጥሩ ነው ….» የሚሉ አስተያየቶች አላየንም። ያለፈበት የተቃውሞና የትችት ፖለቲካ !!!!
በሌላ በኩል «አገር ቤት ያለው ትግል ቢያንስም ቢበዛም ከሕዝቡ ጋር ሆኖ የሚደረግ ትግል ስለሆነ ያዋጣል። መድረኩ መኢአድ የመሳሰሉ ድርጅቶች የራሳቸው ስህተቶች ቢሰሩም፣ ስህተቶቻቸውን እንዲያርሙ እያገዝን፣ ችግር ፈጣሪዎች ሳይሆን መፍትሄ አምጭዎች በመሆን፣ የሚከፍሉት መስዋእትነት በማክበር፣ ትግሉ አንድ እርምጃ እንዲሄድ ማድረጉ ይበጃል» የምንል አለን።
አንድ ወዳጄ በቃሌ ፓልቶክ ክፍል «የማልደርስበት የተሰቀለ ስጋ አለ እያሉኝ ሥጋ በመጠበቅ በረሃብ አልሞትም። ጠረቤዛ ላይ ያለውን ዳቦ እበላለሁ። ያኔ ስጋውን ከተሰቀለበት አውርደው ሲያመጡልኝ ያኔ እንነጋገራለን» ነበር ያለው። ትልቅ አባባል !
«መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፣ ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ» አልነበረ የተባለው። የከረንት አፌር ቡድን እንዲሁም የሚያገለግሉት የግንቦት ሰባት ንቅናቄ፣ የሚናገሩትን ብናዳምጣቸው ፊታውራሪ ገበየሁና ደጃች ባልቻ የተናገሩ ነው የሚመስሉት። «ወያኔን አፍንጫውን ነው ማለት ያለብን። ወያኔ ሊወደቅ ትንሽ ነው የቀረው። ወያኔ አልቆለታል…» ይሉናል። አንዳንዶቹማ ስማቸውን እንኳን በይፋ ለመግለጥ ፈርተው በኒክ ኔም በሳይበር የሚገለጡ የፓልቶክ አርበኞች ናቸው። «ታድያ እኮ እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ ስቲቭን ቢኮ ያስተማሩን ሌላ ነው። በሠላም ይመረጣል ካልሆነም በሰደፍ እንጅ ኩታ አቀብሉኝ ዓይኔን ልሸፍን አልወጣቸውም» ነው አቶ ይልማም ያሉን። እንግዲህ አቶ ይልማ እራሳቸው ሰደፉን ይያዙት ያሳዩና። እኛም ያኔ እንከተላቸዋለን።
አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። በአገራችን ለውጥ እንዲመጣ ከወሬ ያለፈ ትግል ያስፈልጋል። ትግል ደግሞ አገር ቤት ሄዶ ሕዝብን ማደራጀት ነው። በውጭ አገር ተቀምጦ የብራቫዶ ንግግር ማብዛት ትግል አይደለም።
እንግዲህ አሁንም አቶ ይልማንና የአቶ ይልማ አይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ወገኖቼ ቻሌንጅ ማድረግ እፈልጋለሁ። ስለ አንድነት ፓርቲ ፤ ስለ ምርጫው ስለ ሰላማዊው ትግል ብዙ ጽፈዋል። ምርጫው ጥቅም የለውም ብለውናል። እስቲ አሁንም መድረኩንና አንድነቱን ለቀቅ ያድርጉና፣ እነርሱ እየደጋገሙ የወያኔ ማንነትን ከማወራት ፖለቲካ ወጥተው፣ አገራችን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስዳትን የነርሱን አማራጭች ያሳዩን። እንጠብቃለን!!
ግርማ ካሣ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ግንቦት 1 ቀን 2002 ዓ.ም.



