ከአዲስ አበባ ወደ የክ/ሀገሩ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚያስጭኑ ነጋዴዎች ሥራቸውን አቁመዋል። በባንክ የነበራቸውን ገንዘብ በማውጣት በየቤታቸው አስቀምጠዋል። ምክንያቱ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ችግር ቢፈጠር ቅድሚያ ጥንቃቄ ለማድረግ ነው። አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ከምርጫው ጋር በተያየዘ የአንዳንድ ተማሪዎችን የፈተና ጊዜ አራዝሟል። በዚህና ይሄን በመሰለው ምክንያት የ6ኪሎ ዩንቨርስቲ ምድረ-ግቢ ከሐሙስ ጀምሮ ፀጥ-ረጭ ብሏል።

 

ይሄም “ተማሪው በጭንቀት ስሜት ፈተናውን ቢፈተን ጥሩ ውጤት ሊያመጣ አይችልም… ከሚለው በጎ እሳቤ የመነጨ ሳይሆን አይቀርም” ይላሉ የዩንቨርስቲው መምህራንና አንዳንድ ተማሪዎች። “ጭንቀቱ የመነጨው ከምርጫው አኳያ ከሆነ እንዴት ሰላማዊ፣ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የጭንቀት መንስኤ ሊሆን ይችላል?” በማለት ይጠይቃሉ የፖለቲካ ታዛቢዎች በበኩላቸው።

 

ሐሙስ ግንቦት 12 ቀን 2002 ዓ.ም ለኢሕአዴግ ልዩ የምርጫ “ጸሎተ-ሐሙስ” ሆኖ ነበር። የ2002 ምርጫ የአደባባይ ቅስቀሳ ማክተሚያ ቀን በመሆኑ የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎችና ከነፃነታችን ይልቅ በልቶ ማደሩ… ይሻለናል ባዮች የምርጫውን “ጸሎተ-ሐሙስ” በጩኸት፣ በዕልልታና በፍጩት … ሲያደምቁት ውለዋል። የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ የደህዴግ፣ የሕውሓትና የግንባሩ የኢህአዴግ በእጅ የሚጨበጡ ባንዲራዎች ተወለብልበዋል። ኢሕአዴግን ወክለው እንወዳደራለን ያሉ ዕጩዎች በቢጫ መደብ ላይ በንብ ስዕል የተወረረ ጃኬት ለብሰው “ንቦዬ …” በሚለው ዘፈን ታጅበው የአዲስ አበባንና ሌሎች የሀገሪቱን ከተሞች ጎዳናዎች ተዘዋውረውባቸዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የየራሳቸውን የምረጡን ቅስቀሳ ለማካሄድ ላይ ታች ሲሉ ተስተውለዋል። ይሁንና በኢሕአዴግ የምርጫ ጸሎተ-ሐሙስ ቀን ከአዲስ አበባ ባሻገር ባሉ እንደ ደ/ብርሃን፣ አርባ ምንጭ፣ነቀምቴና ሌሎች ከተሞች የተቃዋሚዎች የምረጡን ቅስቀሳ ታውኳል፡።ይልቁንም “በምርጫው ማግስት ችግር ይገጥማችኋል” የሚል ዛቻ ተሰንዝሮባቸዋል።

 

የምርጫ ታዛቢዎችም በአንዳንድ ቦታዎች ቆመጥና ጡጫ እየቀመሱ ወደ አዲስ አበባ ተሸኝተዋል። ራሳቸው በየነ ጴጥሮስ “ከደቡብ ኢትዮጵያ ሃድያና አካባቢው ወደ አዲስ አበባ ስመለስ በፍርሃት ስሜት ውስጥ ሆኜ ነው…” ብለዋል።

 

ኢንጂኒየር ኃይሉ ሻውል ደግሞ “የፈረምነው የምርጫ ሥነ-ምግባር ሕግ አንድም ጊዜ በተግባር ላይ አልዋለም። የኢሕአዴግ ሰዎች የዕብድ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ታዝበናል …” የሚል ቅሬታ አቅርበዋል።

 

ሐሙስ ግንቦት 12 ቀን አዲስ አበባ ከፍተኛ የፀሐይ ሙቀት ነበር። ኢሕአዴግ ደግሞ ከልክ በላይ በሆነ መንገድ ቅስቀሳውን አጋግሎት ታይቷል። በሁኔታው የተበሳጩ የአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች “ንቦዬ…” የሚለውን ዘፈን ተከትለው “ዝንብዬ፣ ጥንብዬ - ማሩ የታል” ሲሉ ተሰምተዋል።

 

ሌሎች ደግሞ ሲፈታተናቸው የሰነበተውን የፍርሃት ጫና ገለል ለማድረግ በመሞከር ስሜት የመድረክ መሪዎች ለቅስቀሳ በወጡበት ጎዳና በተለይም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በተዘዋወሩባቸው ሥፍራዎች የዕጅ መዳፋቸውን በማሳየት ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ እስከመግለጽ ከእልህ የመነጨ የድፍረት ስሜት ድረስ ተጉዘዋል። የድፍረት ስሜቱ የመነጨው፤ ኢሕአዴግ ለማድረግ ከፈለገው መረን-የለሽ የቅስቀሳ ሂደት መሆኑ ተረጋግጧል። ሕዝቡን ለቲሸርት፣ ለደረት ዓርማና ለስክርቢቶ፣ ለኮፍያ፣ ለፖስተር፣ ለባንዲራና ለውሎ አበል … የወጣው ወጪ ብቻ አስቆጥቶታል።

 

ከሰኞ-ሐሙስ ባሉት ጊዜዎች ውስጥ ብቻ በታዩት የአደባባይ ቅስቀሳዎች በዝቅተኛ ግምት ከፍ ሲል ለተገለጹት ጉዳዮች (የኢሕአዴግ የምርጫ ዘመቻ ዝክንትሎች…) ገዥው ፓርቲ ሩብ ቢሊዮን ብር ገደማ አውጥቷል። ይህም ገንዘብ በኢትዮጵያ አቅም ቢያንስ አንድ ዘመናዊና ለደሃው ሕዝብ አግልግሎት መስጠት የሚችል ሆስፒታል መገንባት የሚችል ነው። ያምሆነ ይህ… ግንቦት 13 የኢሕአዴግ ምርጫ ሥነ-ሥቅለት ነው። ከማለዳው እስከ ረፋዱ በዋዜማው ሲጮኽባቸው… የነበሩት የአዲስ አበባ አደባባዮች ፍፁም የመቀዝቀዝ ሁኔታ ይታይባቸዋል። ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ደግሞ ልፈፋው… የአምባገነኑን መንግሥት ፈጣሪ ፓርቲ ለአሸናፊነት መዘጋጀት ነው። ቅዳሜ ግንቦት 14 የምርጫው ቅዳም-ሹር ነው። ዕሁድ ግንቦት 15 ቀን ኢሕአዴግ እጅግ በጣም ብዙ የሠላምና የተዓማኒነት ቃላት ያዝጎደጎደለት የ2002 ምርጫ ትንሳኤ ይሆናል።

 

ነገ ዕሁድ ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ ይካሄዳል። ዓርብ ግንቦት 13 ቀን 2002 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከተማዎች ከፍተኛ ዋት ካላቸው የላውድ ስፒከር ድምጽ ጩኸቶች፣ ከአውቶሞቢል ክላክሶች ረብሻ፣ ከኢሕአዴግ ደጋፊ-አጫፋሪዎች ዳንኪራ ፀጥ-ረጭ ብለው ውለዋል። ዕለቱ የምርጫ 2002 ኢሕአዴግ ሥነ-ስቅለት የሚከበርበት ዕለት መስሎ ውሎአል። ክርስቲያኖች የጌታቸውን መሰቀል በአርምሞ እንደሚያስቡ… የሕውሓት ሰዎችም “ኢሕአዴግ በምርጫው ያገኛል የሚሉትን ልማታዊ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታዓማኒ ትንሳዔ” በናፍቆት የሚጠብቁት ይመስላሉ።

 

ከሕውሓት ኢሕአዴግ አባላትና አጫፋሪዎች ባሻገር ያሉት ኢትዮጵያውያን ግን በሐቅ የሚጠብቁት የሰውነታቸውን ነፃነትና ክብር፣ የሀገራቸውን አንድነትና የይቅር መባባሉን … ዘመን ትንሳዔ መግባት ነው። እንዲሁም ሆኖ በምርጫ 2002 ሥነ-ስቅለት፤ ግንቦት ወር እንደመጀመሪያው ሳምንት በመዲና አዲስ አበባ ዕርጥብ አየሩን ጀባ አላደረገም። በአብዛኛው ንዳዱን ያወርደዋል። በዚህ ላይ የቀረውን የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ እንዳያደምጥ የፈለገው መንግሥት ጣቢያውን አርብ ዕለት አፍኖታል።

 

የተፈጥሮ ዑደት በመሆኑ… የቅዳሜ ጀንበር ወጥቷል። የአርብ ፀሐይ ጠልቋል። ግንቦት 14 ቀን 2002 ዓ.ም የሀገር አቀፍ ምርጫው ቅዳም ሹር ነው።

 

ከተማዎች በዝምታ ድባብ ተውጠዋል። ቅዳሜ የዘውትሩን ቅዳሜ አይመስልም ኢትዮጵያ ውስጥ። ልዩ ድብታ አለበት። ከአዲስ አበባ ከተማ ባሻገር “ተቃዋሚዎች” የሚባሉት ያለ ምርጫ ታዛቢ ነው የሚወዳደሩት። ምነው? ቢሉ ታዛቢዎቻቸው ሁሉ ተባረዋል። አሳዳጊዋን እንዳጣች ውሻ… ተዋክበዋል። እንደዚህ መሆኑ በተለይ “ኦሮሚያ” በሚባለው የኢትዮጵያ ግዛት ሙሉ በሙሉ ርግጥ ነው። ታዲያ የተቃዋሚዎችን ድምጽ የሚታዘብላቸው ማነው? ምናልባት የአውሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድን አባላት ሊሆኑ ይችላሉን? አይታወቅም። የሚታወቀው… የተቃዋሚዎቹ ምርጫ ታዛቢዎች ዱላና ጡጫ እየቀመሱ፣ አነስ ሲልም ዛቻና ማስፈራሪያ እየተቀበሉ “ልንታዘብ ነበር…” ካሉበት የምርጫ ጣቢያ ሁሉ መባረራቸው ነው።

 

ሌላው ፖሊስ በተስጠው ልዩ መመሪያ መሠረት ጠመንጃውን በግምጃ ቤቱ አስቀምጦ፤ ሁለት፣ ሦስትና አራት… ሆኖ፣ ቆመጥ አንግቦ፣ በጸጥታ!.. ለጸጥታ ማስከበር ተግባር እየተንጎራደደ ነው። “አንድም ፌደራል ሆነ ሌላ ፖሊስ መሣሪያ ይዞ በሕዝብ መሀል እንዳይታይ… በምርጫው ዋዜማና በምርጫው ዕለት” የሚለው መመሪያ ተግባራዊ ሆኖ ነው መሰል፤ የቅዳም-ሹር ዕለት በአዲስ አበባ የሚታየው ሁኔታ ይኸው ነው። ግን በስውር የታጠቁ ሲቪል የደህንነት ሰዎች መኖራቸውን የፖሊስ ምንጮች ራሳቸው ይናገራሉ።

 

አይሆንም እንጂ ምርጫው ረብሻ … የሚፈጥር ከሆነ፣ አልሞ መቺው ልዩ ኃይል ካደፈጠበት ወጥቶ ርምጃ የሚወሰድ ለመሆኑ የሚጠራጠር ካለ እሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልነበረ ነው። መለስ ዜናዊ መመሪያ አወርደዋል። በመመሪያው መሠረት “ልዩ ኃይሉ” ከየመሸገበት ካምፕ ወጥቶ ወደ ተጠራበት ሥፍራ እንደነብር ሊወረወር መቻሉን መጠራጠር ሞኝነት ብቻ ነው። “በቢለዋ ቀልድ የለም አለች ዶሮ” ሲሉ መለስ የዘበቱትን አለመዘንጋት ብልህነት ይሆን? ...ግን ለምን ይሆን የኢሕአዴጉ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ጠዋት ማታ “ሰላም ይሁን ምድሩ ሁሉ! ...” የሚለውን ዜማ ደጋግሞ የሚያሰማው? ይህ ዜማ በወታደራዊው መንግሥት ብርክ የያዘው ሰሞን ተመላልሶ ይሰማ ነበር። ነገ ዕሁድ የምርጫ 2002 ትንሳዔ ነው። እሱም ስለራሱ ራሱ ያውቃል።

 

ኮርጆዎች ካልታዘቡ በቀር ማን ማንን እንደመረጠ “ተዓማኒ” ምስክርነት የሚሰጥ አይገኝም። ምርጫው ያለበት ችግር እንዳለ ሆኖ ያለችውን ቀዳዳ ተጠቅመው መሳሪያ፣ ኃይል፣ ጉልበት፣ ማን አለብኝነት ... የተጠናወተውን አምባገነን አገዛዝ ከማርበድበድ አለፎ በሀገሪቱ ያለውን ችግር ፊት ለፊት ተጋፍጠው የሚፋለሙ ተቃዋሚዎች ምስጋና ሲያንሳቸው ነው። እነሱ በዚህ ምርጫ ሽር ጉድ ባይሉ ያለፈውን አንድ አመት ምን ይውጠን ነበር። ያም ሆነ ይህ፣ ይህም ሆነ ያ … ምርጫ 2002 እንደምርጫ 97 አይደለም። የራሱ የሆነ መልክና ምናልባትም ደም-ግባት ይኖረዋል። ይሔን ጥንቅር እያነበባችሁ ምርጫው እየተካሄደ ሊሆን ይችላል። ተጠናቆም ይሆናል። የምርጫውን ትንሳዔ ወሬ በምርጫው ማግስት የሚሆነውን አብረን እናያለን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ